ከሀምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል መስራች ዶክተር ካትሪን ሀምሊን ለሙያ መሰጠትንና በጽናት መቆምን ተምረናል -የጤና ባለሙያዎች

236

ግንቦት 22/2011 ለሙያ መሰጠትንና በጽናት መቆምን ከሀምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል መስራች ከሆኑት ዶክተር ካትሪን ሀምሊን  መማራቸውን በሆስፒታሉ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ገለጹ።

ከ60 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዶክተር ካትሪን ሀምሊን የፌስቱላ ህመም ያጋጠማቸው ሴቶችና ህጻናት ህመምና ስቃይ በመገንዘብና በህክምና በኩል ያለውን እጥረት በማየታቸው ከባለቤታቸው ጋር የህክምና አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፤ በዚህም ከ60 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ማዳን ችለዋል።

ዶክተር ካትሪንና ባለቤታቸው ዶክተር ሬጂናልድ ሀምሊን ላበረከቱት አገልግሎት መታሰቢያ ሀውልት በሆስፒታሉ ውስጥ ተሰርቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በተገኙበት ተመርቋል።

በምርቃቱ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹት የጤና ባለሙያዎች እንደተናገሩት የአውስታራሊያ ዜጋ የሆኑት ዶክተር ካትሪን  ሀምሊን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ላለፉት 60 አመታት በፌስቱላ ህመም ሳቢያ ለከፍተኛ ህመም የተጋለጡና በህብረተሰቡ መገለል የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናት ህይወት የታደጉ ባለሙያ ናቸው።

የጤና ባለሙያዎቹ እንደገለጹት ከዶክተር ሀምሊን ለሙያ መሰጠትንና በጽናት መቆምን፣ ሰብዓዊነትን፣ የስራ ክብርንና በህይወት ውስጥ መልካም ስራ ሰርቶ ማለፍን ተምረዋል።

የውጭ አገር ዜጋ የሆኑት ዶክተር ሀምሊን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለዘርና ማንነት  ቦታ ሳይሰጡ ስለ ሰብዓዊነት በመስራታቸው ኢትዮጵያውያን ከእሳቸው በርካታ መልካም ነገሮችን ሊማሩና በብሄር በመከፋፈል ከመጋጨት ሊቆጠቡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዶክተር የሺነሀ ደምረው የፌስቱላ ቀዶ ህክምና ሀኪምና የሆስፒታሉ ተጠባባቂ ሜዲካል ዳይሬክተር 

እንዳሉት "በመጀመሪያ ደረጃ እራስን መስጠት እንዳለብን ነው ትልቁ ነገር ከእሳቸው የተማርነው። ከሰለጠነ ሁሉ ነገር ከሞላበት አገር ነው የመጡት ፤ሲጀምሩ ቀላል አልነበረም ግን ደግሞ አልተሸነፉም ሳይሸነፉ እዚህ ደረጃ ደርሰዋል እና አንድ ባለሙያ እራሱን አሳልፎ ከመስጠት ድረስ መድረስ አለበት። እንደገናም ደግሞ በጽናት መቆም አለበት የሚለውን ነገር ነው ያስተማሩን" ብለዋል። 

"ከዶክተር ሀምሊን ብዙ ነገር ነው የተማርነው ጥንካሬን፣ ሀገር እንድንወድ ወገናችንን እንድንወድ በተግባር በስራ የተማርኩት ትምህርት ሊለውጠኝ ይገባል " ሲሉ የተናገሩት የነርሶች ኃላፊ ውዴ ፋንታሁን  ናቸዉ፡፡

ዶክተር ካትሪንና ባለቤታቸው ዶክተር ሬጂናልድ ሀምሊን ላበረከቱት አገልግሎት ለተሰራላቸው የመታሰቢያ ሀውልት ምርቃት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  ባደረጉት ንግግር ዶክተር ካትሪን "ከዘር ፣ ከሃይማኖት፣ ከብሔር በላይ ሰው መሆን እንደሚበልጥ ያሳዩና የ60 ሺህ ሰዎችን ህይዎት ያዳኑ ጀግና እናት " መሆናቸውን ተናግረዋል።

እኛ ኢትዮጵያዊያንም ሳንከፋፈል እንደ  ሰው ሆነን መኖርና ታሪክ መስራት እንደሚኖርብን ለመማር "የእሳቸውን ልምድ መውሰድ ይኖርብናልም " ብለዋል።

የህምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በመቀሌ፣ ባህርዳር፣ይርጋለም፣ ሀረር እና በመቱ ከተሞች ቅርንጫፎች በመክፈት እየሰራ ይገኛል።

ከህክምና አገልግሎት በተጨማሪ ኮሌጅ በመክፈት የአዋላጅ ነርሶችን በማሰልጠንና በክልሎች በመመደብ የፌስቱላ ህክምና ተደራሽነት ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም