ኢትዮጵያና ኩባ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ

133

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2011 ኢትዮጵያና ኩባ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተስማሙ።

የኩባ ምክትል ፕሬዘዳንት ሳልቫዶር አንቶኒዮ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን ከውጭ ጉዳይ  ሚኒስትር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋርም በዛሬው እለት መክረዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በምክክራቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን የበለጠ ለማጎልበት መስማማታቸውም ታውቋል።

ውይይታቸውን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት ባለስልጣናቱ  ሁለቱ አገራት በቀጣይ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ ተስማምተዋል።

የኩባው ምክትል ፕሬዘዳንት ሳልቫዶር አንቶኒዮ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ከዚህ ቀደም በአለም አቀፍ መድረኮችና ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ትብብር ጥሩ ውጤት ያመጣ መሆኑን አስታውሰዋል።

በቀጣይም ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትስስር አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም