ፍርድ ቤቱ በአቶ በረከትና አቶ ታደሰ ክስ የአቃቢ ህግ ምስክሮችን ማዳመጥ ጀመረ

96

ግንቦት 21/2011 የቀድሞ የጥረት ኮርፖሬት አመራሮች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በተከሰሱባቸው የሙስና ክሶች የህግ ጠበቃ አቁመው መከራከር ጀመሩ፡፡ 

በተከሰሱባቸው የሙስና ጉዳዮች 13 የሰው ምስክሮች ቀርበው ዛሬ መደመጥ ጀምሯል፡፡

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ የሚገኘው ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም በጠበቆቻቸው ላይ በሚደርሰው እንግልት በጠበቃ መከራከር አልቻልንም በሚል አቤቱታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ያቀረቡትን አቤቱታ በመቀበልም ጠበቆችን ለይተው እንዲያሳውቁና ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግ ፍርድ ቤቱ ባለፈው በዋለው ችሎት ተዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በዛሬው እለት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለችሎቱ የህግ ጠበቃ ይዘው ሊቀርቡ መቻላቸውም ታይቷል፡፡

ለቀረቡት የህግ ጠበቃም በሚያርፉበት ሆቴል፣ ደንበኞቻቸውን ለማግኘት ወደ ማረሚያ ቤት ሲጓዙና ከኤርፖርት ወደ ፍርድ ቤት ሲጓጓዙ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ታዟል።

ተከሳሾቹ አሰራርን በማያመች ሁኔታ በመምራት ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል አራት ክስ ተመሰረቶባቸው ቆይቷል፡፡

በቀረቡባቸው ክሶችም ወንጀሉን አልፈፀምንም ሲሉ ሁለቱም ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በተከሰሱባቸው የሙስና ወንጀሎች የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ 13 የሰው ምስከሮችን አቅርቦ ዛሬ ማሰማት ጀምሯል፡፡

ዛሬ ከጥዋት ችሎቱ የአንድ ሰው ምስክር መስማት የቻለ ሲሆን ከሰዓት፣ ነገ እና ከነገ ወዲያ ሁሉንም ምስክሮች ለማሰማት ችሎቱ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ከሁለቱ ተከሳሾች ጋር ተከሰው የቀረቡት አቶ ዳንኤል ግዛው ዛሬ ጠበቃቸው ባለመቅረቡ ለነገ ይዘው እንዲቀርቡና ምስክሮች መመስከር እንዲችሉ ተእዛዝ ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም