አዲሱ የአምቦ አውቶብስ መናኸሪያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስራ ይጀምራል…የከተማው ትራንስፖርት ባለስልጣን

198

አምቦ ግንቦት 21/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ በ56 ሚሊዮን ብር በጀት ግንባታው በመካሔድ ላይ ያለው የአምቦ ዘመናዊ የአውቶብስ መናኸሪያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስራ ይጀምራል ተባለ።
የአምቦ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ቦጃ ወልደ ሚካኤል እንደገለጹት በ12 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ በያዘው ቦታ ላይ እየተገነባ ያለው መናኸሪያ የቢሮ ሕንጻ የተገልጋይ ማረፊያ፣ካፌ፣የመረጃ ማዕከልና ለመንግደኞች መስተንግዶ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች የተሟሉለት ነው።

ከሶስት አመታት በፊት የግንባታ ስራው የተጀመረው የአምቦ አውቶብስ መናኸሪያ ባለፈው ዓመት ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ቢታቀድም በተቋራጩ አቅም ማነስ ምክንያት ስራው መጓተቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ የግንባታው ስራ ከ95 ከመቶ በላይ መጠናቀቁን ገልጸው “አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል” ብለዋል ፡፡

መናኸሪያው ቀደም ሲል በከተማው ይታይ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንደሚያቃልል ገልጸዋል። 

የአዲሱ መናኸሪያ መገንባት የትራንስፖርት አገልግሎትን ከማሳለጥ ባለፈ የንግዱን እንቅስቃሴ በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ የገለጹት ደግሞ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ካንቲባ አቶ ተረፈ በዳዳ ናቸው።

“ግንባታው በአሁኑ ወቅት ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለ700 ወጣቶች ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥራል”ብለዋል።

በአካባቢው የሚኖር ወጣት ኒሞና ፈይሳ በበኩሉ የመናኸሪያው መሰራት ለሱና ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር እምነቱን ገልጿል፡፡

በአምቦ ቀበሌ 02 አካባቢ የተገነባው የአውቶቢስ መናሃሪያ በአንድ ጊዜ እስከ 600 አሽከርካሪዎችን ማስተናገድ እንደሚችል ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡