የህብረት ስራ ማህበራት ለህዝቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጠንክረው መስራት አለባቸው--የአማራ ክልል ም/ፕርዚዳንት

129

ግንቦት 21/2011 “የህብረት ስራ ማህበራት ግብይት ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ሃሳብ ሶስተኛው ክልል አቀፍ ኢግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም በባህርዳር  ከተማ ተጀምሯል።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የህብረት  ስራ ማህበራት  በግብርና  ላይ ለተመሰረተው የሃገራችን  ኢኮኖሚ እድገት ተኪ  የለሽ ሚና  እየተጫወቱ  ይግኛሉ።

በዚህም ማህበራቱ የግብርና ምርት እድገት እንዲፋጠንና የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ አምራቹንና ሸማቹን በማገናኘት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ መሸጋገር የጀመሩትንም ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የክልሉ ህብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለልኡል ተስፋ በበኩላቸው ሃገራችን ከድህነትና ኋላ ቀርነት እንድትላቀቅ የህብረት ስራ ማህበራት ግንባር ቀደም ሚናቸውን እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ጠንካራና ዘላቂነት ያለው የገበያ ትስስር እንዲፈጠርም ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ ሌሎች ተግባራትን በማከናወን የአርሶ አደሩን የምርቱ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ” ነው ብለዋል።

የሚስተዋልባቸውን የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እጥረት እንዲሁም የመብራት ችግሮች እንዲፈቱ በየደረጃው ያለ አመራር ኃላፊነቱን ወስዶ ሊፈታ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዛሬ በፓናል ውይይት በተጀመረው በዚህ ዝግጅት ላይ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልልና ወረዳ ባለው አደረጃጀት ላይ የሚገኙ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች፣የማህበራት ተወካዮችና ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም