በምዕራብ ሐረርጌ ሁለት ወረዳዎች የተከሰተ የአተት በሽታ ጉዳት እያደረሰ ነው

143

ጭሮ ግንቦት21/2011በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በጭሮ እና በኦዳ ቡልቱም ወረዳዎች  በተከሰተ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት (አተት) በሽታ የሦስት ሰዎች ሕይወት  ሲያልፍ 42 ሰዎች በበሽታው ተጠቂ መሆናቸውን የዞኑ ጤና ቢሮ መምሪያ ገለጸ።

የኦዳ ቡልቱም ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልዪ አህመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት በወረዳው ኩሉ ቀበሌ በተከሰተው በሽታ እስከ አሁን የሶስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 34 ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል።

በሽታው ወደ ሌሎች ቀበሌዎች እንዳይዛመትም አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸው መነሻ ምክንያቱ በአካባቢው ካለው የንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት ጋር ተያይዞ ሰዎች የዝናብና የኩሬ ውሃ በመጠቀማቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

ለህሙማኑም በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ተዘጋጅቶ አስፈላጊውን ክብካቤና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሽታው በተከሰተበት አካባቢ ሰዎች ንጽህናቸውን በጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች እንዲገለገሉና ውሃን በኬሚካል በማከም እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የጭሮ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን በድሪ ናቸው።

የአተት በሽታ በወረዳው ኮሎሎ ቀበሌ በስምንት ሰዎች ላይ መገኘቱን ገልጸው በአሁኑ ሰአትም ለተጠቂዎች ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ በማዘጋጀት የህክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ ጤና ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመዲን አህመድ በበኩላቸው “ወቅቱ የአተት በሽታ የሚከሰትበት እንደመሆኑ ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።

በሽታው የተከሰተባቸው ወረዳዎች ላይ በህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እና ባለሙያዎችን ወደ ቦታው በመላክ እገዛ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሽታው ወደ ሌሎች የዞኑ አካባቢዎች እንዳይዛመትም የቅድመ መከላከል እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰጠት መጀመሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም