ሴቶችና ወጣቶች ለሃገር አንድነት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

79

ጋምቤላ  ግንቦት 21/2011 የሴቶችንና ወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለአገር አንድነት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ።
የኢፌዴሪ ሴቶች፡ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በጋምቤላ ክልል ሲያካሂድ  የነበረው የመስክ ጉብኝትና የመድረክ ውይይት  ተጠናቋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሴቶችንና የወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት ማሳደግ አንዱ መፍትሄ ነው።

በተጨማሪም የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ለማጎልበት በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት እንዲሁም የልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚወጡ ህጎችንና ደንቦችን ከማስፈጸም አኳያ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ፡ወጣቶችና ማህበራዊ ጎዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ወይዘሮ ፋኑ ደቻሳ በሰጡት አስተያየት ከወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ፡ከመስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲሁም ከብድር አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው ስራዎች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።

ከዚህም ባለፈ የሴቶችን ማህበራዊኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጽዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚታየው የሴት ልጅ ግርዛት እንደገና እያንሰራራ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ችግሮችን ለመፍታት የሴቶችንና የወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት ማሳደጉ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ እንዳሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወጣቶችን በማቀራረብ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት ዝቅተኛ ነው።

“ግጭቶችና አለመግባባቶች በሚነሱበት ጊዜ የሴቶችና ሕጻናት የአደጋው ተጎጂነት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እነዚህን ችግሮች በመፍታት የሀገር አንድነትን ለማጠናከር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል፡፡

የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት ሚና በተለይም በክልልና ከዚያ በታች ባለው የአመራር እርከን ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አፀደ አይዛ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ለአመራርነት የሚበቁ ብዙ ሴቶች ቢኖሩም ከክልል ጀምሮ ባሉት የአመራር ሰጪነት ቦታዎች ላይ ያሉ ሴቶች በቁጥር አናሳ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት እርከኖች ጋር በቅንጅታዊ ስራ ሴቶች በተሻለ ወደ ውሳኔ ሰጪነት የሚመጡበትን እድል ማሳደግ እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

ወይዘሮ አሚር አብዱልከሪም የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው የሴቶችንና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚወጡ ህጎችንና ደንቦችን ተፈጻሚ ከማድረግ አኳያ ችግሮች መኖራቸውን በመጠቆም በቀጣይ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አመላክተዋል።

የህጻናትን መብት በማስከበር ረገድም በተለይም ከዚህ በፊት ለውጭ ጉዲ ፈቻ የተሰጡ ህጻናትን ቤተሰብ ጋር ከማገናኘትና ደህንነታቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ቅንጅታዊ ስራውን በማጠናከር ህጻናቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን እድል መፍጠር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ እንዳሉት የሴቶችንና የወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣት ማህበራትን ከማጠናከር ባለፈ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

ከዚህም ባለፈ የወጣቶችን የውሳኔ ሰጪነት ለማሳደግ ከተለያዩ ክልሎች ለተወጣጡ ከ250 በላይ ወጣቶች በአመራርነት ላይ የተመሰረተ ሥልጠና መሰጠቱንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሃገሪቱን አንድነት በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ አንድነትን ከማጎልበት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ መታየታቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ የሴቶችን የህጻናትንና የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ትላንት ምሽት ላይ የተጠናቀቀው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወራት የስራ ክንውን ግምገማ መድረክና የመስክ ጉብኝት ላይ ከፌዴራል ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም