መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አባላት ችግኝ ተከሉ

113

ግንቦት 20/2011 መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ችግኝ ተከሉ።

በችግኝ ተከላ ስነስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በችግኝ ተከላ ስነስርዓቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አምባሳደሮች በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ አሻራቸውን ማሳረፍ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አምባሳደር ጂያን ንጋንዱ ኢሉንጋ ''እኔም ሆንኩ ሌሎች የስራ ባልደረቦቼ የሆኑት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በዚህ ሁነት በመሳተፋችን ደስተኞች ነን'' ብለዋል።

በመጪው ክረምት ውስጥ አራት ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ ለመትከል የተያዘው ዕቅድ እጅግ በጣም አዎንታዊ የሆነ ውጤት እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር የሆኑት ቦርጃ ሞንቴሲኖ ማርቲኔዝ ዴል ሴሮ በበኩላቸው በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ አሻራቸውን ማሳረፍ መቻላቸው ደስታ የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም ዙሪያ ብዙ ወዳጅ ያላት ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃን ለማከናወን የምትወስደውን ርምጃ ሁሉም እንደሚደግፈው ተናግረዋል።

አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በመንግስት የተያዘው ዕቅድ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመዋጋት ከሚከናወኑ ተግባራት ቀዳሚው መሆኑን አመልክተዋል።

በብሔራዊ የአረንጓዴ ልማት የድርጊት መርሐ ግብር በመጪው የክረምት ወቅት አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከት የሚያስችል መርሃ ግብር ወጥቶ ቅድመ ዝግጅት ተከናውኗል።

በዚህ መርሐ ግብር 40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ ለመትከል ታቅዷል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም