ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሱዳንን በጊዜያዊነት ከሚመራው ወታደራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጋር ተነጋገሩ

71

ግንቦት 20/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሱዳንን በጊዜያዊነት እያስተዳደረ ከሚገኘው ወታደራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ ኤል-ቡርሃን ጋር ተነጋገሩ።

ሊቀመንበሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

ከችግኝ ተከላው በኋላ በሁለትዮሽ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊ እንደገለጹት፤ ሱዳናውያን በአሁኑ ወቅት የሚገኙበትን ሁኔታ ለማሻሻል ሁሉን አካታች በሆነ መንገድ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ኢትዮጵያም በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የማትገባ መሆኗን አረጋግጠውላቸዋል።

ሱዳንን በጊዜያዊነት እያስተዳደረ የሚገኘው ወታደራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ ኤል-ቡርሃንም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ሱዳንን ለ30 አመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ባለፈው ሚያዚያ መጀመሪያ በአገር ውስጥ የተነሳባቸውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊቱ ከስልጣን እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ በጊዜያዊነት ስልጣን የያዘው መከላከያ ምክር ቤቱ ስልጣኑን ለሲቪል እንዲያስረክብ በተቃዋሚዎች ግፊት እየተደረገበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም