የግንቦት 20 ድል በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና አለው...ዶክተር ደብረጽዮን

96

አክሱም ግንቦት 20/2011 የግንቦት 20 የድል በዓል ኢትዮጵያ በህግ-መንግስትና በዴሞክራሲያዊ ስርአት እንድትመራ ያስቻለ ነው ሲሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ፡፡

28ኛ ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓልን በክልል ደረጃ ‘‘ግንቦት 20 የጽናት፣ የአይበገሬነትና የአሸናፊነት አርማ ነው‘‘በሚል መሪ ቃል በአክሱም ከተማ በደማቅ ስነ-ስርአት ዛሬ ተከብሯል።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት የግንቦት 20 ድል በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግል የተገኘና የሁሉም ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ተረጋግጦ በማንነታቸው እንዲኮሩ ያስቻለ ነው።

ድሉ የራስን አስተዳደር በራስ የመወሰን መብት እና የመልማት እድል የከፈተ መሆኑን እና ሁሉም ክልሎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል እንዲወስኑ ያስቻለ መሆኑንም ነው ያስታወቁት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ።

ድሉ የሁሉም ህዝቦች ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ እንዲያድግ፣እኩልነትና ፍትሓዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከማድረጉም ባለፈ  በህገ-መንግስት የምትመራ ዴሞክረሲያዊት ሀገር ለመገንባት እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

“ዛሬ ላይ ባለፉት 28 አመታት የተገኙ ድሎችን በመካድ በተለይ ፌዴራላዊና ህገ-መንግስታዊ ስርአትን ለማፍረስ የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

“የተገኘውን ሁለንታዊ ለውጥ እና ድል መጠበቅ ያስፈልጋል” ያሉት ምክትል ርእሰ-መስተዳድሩ በተለይ የትግራይ ህዝብ የያዘውን ሰላም የማስከበር ጠንካራ አቋሙን ማስቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል።

28ተኛው የግንቦት 20 ድል ሲከበር የፌዴራል ስርዓቱ ላይ የተደቀኑ ስጋቶችን ለማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ የሚቆምበት እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በመልእክታቸው ላይ አንዳሉት የ2012 ሃገር አቀፍ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ሁሉም መዘጋጀት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የግንቦት 20 ድል ከኤርትራውያን ጋር በጋራ  መስዋዕት የተጻፈ ታሪክ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ደብረጽዮን በሁለቱ ሃገራት መካከል የተጀመረውን የሰላም ጉዞ ለማስቀጠል የክልሉ መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በበዓሉ ከተሳተፉት የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙሉአለም ግርማይ እንዳሉት፣ኢትዮጰያ ውስጥ በግንቦት 20 የተገኙ የሰላም፣ የአንድነትና የመከባበር እሴቶችን ማስቀጠል ይገባል።

“በማንነታችን እንድንኮራ ፣ባህላችንንና ቋንቋችን እንድናሳድግ ያደረገን በግንቦት 20 የተገኘው ድል ነው” ብለዋል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የውቅሮ ከተማ ነዋሪ ወጣት በሪሁ ጸጋይ በበኩሉ፣ድሉ ወጣቶች ፖተሊካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ያደረገ መሆኑን ገልጿል።

“የሀገሪቱ ሰላምና አንድነት የሚረጋገጠው በወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እና በበሳል አስተሳሰብ ነው” ያለው ወጣቱ በሪሁ፣የሰማእታትን አደራ በመቀበል በክልሉ ያለውን ሰላም ፣አንድነት እና ልማት ለማስቀጠል የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም