ድሬዳዋን ፅዱና ውብ መኖሪያ በማድረግ ተቋማት ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ

54

ድሬዳዋ ግንቦት 20/ 2011 ድሬዳዋን ፅዱና ውብ ከተማ ለማድረግ ተቋማት ድርሻቸውን እንዲወጡ የአስተዳደሩ ጽዳትና ውበት ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ።
ኮካ ኮላ ኩባንያው ''ዛሬን እንሰብስብ ነገን እናትርፍ!'' በሚል መሪ ሃሳብ ከተማዋን ከፕላስቲክ ጠርሙሶች የማፅዳት ዘመቻና የኅብረተሰብ ንቅናቄ መርሐ ግብር ትናንት መተግበር ጀምሯል።

የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ አቶ ጣሂር ሮብሌ  በከተማዋ ድርጅቶችና ፋብሪካዎችም መርሐ ግብሩን ለማሳካት ድርሻቸውን እንዲወጡ  ጠይቀዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ከተማውን በማቆሸሽና የጎርፍ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት ችግር የሚፈጥረውን የፕላስቲክ ጠርሙስ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ኤጀንሲው ችግሩን የሚፈቱ ዘመናዊ አደረጃጀቶችና አሠራሮች ከመዘርጋት በተጨማሪ በቁሳቁስና በሰው ኃይል ለማሟላት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከከተማዋ በቀን የሚመነጨው 147 ቶን ቆሻሻ በዓይነትና በመጠን እየጨመረ በመምጣቱና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎተ ዘመናዊና ተደራሽ ባለመሆኑ ለፅዳቷ መበላሸት ግንባር ቀደም ምክንያት መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የኮካኮላ ኩባንያ የህግና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ንጉስ ዓለሙ በበኩላቸው ኩባንያው በራሱ ተነሳሽነት የፅዳትና የአካባቢ ብክለት የሚፈጥረውን የፕላስቲክ ጠርሙስ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል መርሐ ግብሩን መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ  በተከፈቱት አራት የፕላስቲክ ጠርሙስ መሰብሰቢያ ማዕከላት ጠርሙሶቹን በማስረከብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡

አቶ መሐመድ አህመድ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ከተማውን እየበከለ የሚገኘውን የፕላስቲክ ጠርሙስ ለማስወገድ እንዳይቋረጥ  መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ብዙአየሁየተባሉት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው  መርሐ ግብሩ  ለሌሎችም ፋብሪካዎች መነቃቃትንና ለወጣቶች ሥራ በመፍጠሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

መርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የፕላስቲክ ጠርሙስ በመሰብሰብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የወጡ ወጣቶች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

አንደኛ በመውጣት የ10ሺህ ብር ሽልማት የተቀበለው የእነወጣት በአፈወርቅ ጌታሁን ማህበር ተወካይ  ሥራ አጥ ወጣቶች በመርሐ ግብሩ ተሳትፈው በሚያገኙት ገቢ አማራጭ ሥራ ለመፍጠር እንደሚያተጋቸው ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም