ምክር ቤቱ የአገሪቷን የ2011 በጀት ዓመት ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴ መራ

76
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የአገሪቷን የ2011 በጀት ዓመት ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ። የሚንስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ለቀጣዩ በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ለምክር ቤቱ መምራቱ ይታወሳል።። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣  30ኛ መደበኛ ስብሳባው የበጀት መግለጫው ቀርቦለት ሰፊ ውይይት አካሄዷል። በውይይቱም የአገሪቷ ያለፉት ዓመታት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጻም፣ የቀጣይ በጀትና የገቢ አሰባሰብ ነጥቦች ላይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል። በዚህም በቀጣይ የአገሪቷ ኢኮኖሚ የ11 በመቶ እድገት እንደሚያመጣና  ባለፉት ዓመታት የታየው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ታሳቢ ያደረገ ረቂቅ በጀት መውጣቱን አስታውቀዋል። በተያዘው በጀት ዓመት የታየው የዋጋ ግሽበትም በቀጣዩ በጀት ዓመት መጨረሻ እየተረጋጋ አንደሚሄድ መገመቱን ጠቁመዋል። በጀቱ ካለፈው ዓመት በጀት አኳያም የ3 ነጥብ6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ዶክተር አብረሃም የተናገሩት። ከረቂቅ በጀቱ ውስጥም 287 ቢሊዮን ብር ያህሉ ከታክስ፣ ከእርዳታና ከብድር የሚሸፈን ሲሆን፤ ቀሪው የበጀት ጉድለት ሆኖ ተመዝግቧል። የታየው የ59 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለትም ከአገር ውስጥ ብድር እንደሚሸፈን ነው ረቂቅ አዋጁ በቀረበበት ወቅት የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም