ዶክተር ወርቅነህ የስካንዲኔቪያ አገራት ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ

72
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የስካንዲኔቪያ አገራት ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ ዶክተር ወርቅነህ ላለፉት ሶስት ቀናት በኖርዌይ፣ ፊንላንድና ዴንማርክ ያደረጉት ቆይታ ስኬታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ አስታውቋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ከውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከአገራቱ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሷል። ዶክተር ወርቅነህ ከአገራቱ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ጋር ያደረጉት ውይይት በሁለትዮሽ፣ በአካባቢያዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ያተኮሩ እንደነበሩ ተገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በፊንላንድ በነበራቸው ቆይታ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን የጉብኝት ግብዣ ለፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቱም ጉብኝቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር አምናለሁ በማለት የጉብኝቱን ግብዣ በደስታ መቀበላቸውን ተናግረዋል። ዶክተር ወርቅነህ በኖርዌይ ባደረጉት ቆይታም ከአገሪቱ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ያራ ኢንተርናሽናል የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የኩባንያው ኃላፊዎች በኢትዮጵያ በግብርናው መስክ መሰማራት እንደሚፈልጉ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ከኖርዌይ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ቋሚ ኮሚቴው ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርግም አስታውቋል። የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ላርስ ሎክ ራስሙሰን ከዶክተር ወርቅነህ ጋር በኮፐንሀገን ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና ኢኮኖሚ የማፋጠን እርምጃዎች አገራቸው እንደምትደግፍ ገልጸዋል። ኖርዌይ፣ ዴንማርክና ፊንላንድ የኢትዮጵያ የልማት ትብብር አጋር ከሚባሉት አገራት በዋንኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም