ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን ኃላፊነታችንን እንወጣለን-የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

73

ድሬዳዋ ግንቦት 19  ቀን 2011 በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት በእርቀሰላም ተጠናቅቆ ዛሬ ትምህርት ተጀምሯል፡፡

በእርቀ ሰላሙ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ጌቱ ገበየሁ ችግሩን በውይይትና በእርቀ ሰላም በመፈታቱ መደሰቱን ገልጿል፡፡

 ''መቼም ቢሆን ተማሪዎች በብሔርና በጎሣ ተቧድነው አይጣሉም።' የሚያጋጥሙ ችግሮች በውይይትና በመቀራረብ መፍታት ይገባናል። ለዚህም ኃላፊነቴን እወጣለሁ'' ብሏል፡፡

''እርቀ ሰላም መፍጠራችን አግባብና ትክክለኛ ተግባር ነው''ያለቸው ደግሞ ተማሪ መልካም ዓለሙ፤ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ሁነቶች በመፍጠር  ግንኙነቱን እንዲያጠናክር  ጠይቃለች።'እኛም ለሰላማዊ መማር ማስተማር ተግባር ኃላፊነታችን እንወጣለን'' ስትልም አስተያያቷን ሰጥታለች፡፡

ተማሪ ዳዊት ጳውሎስ በበኩሉ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላም እንዲኖር ሁሉም የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንዳለበት አመልክቶ፣ ይህም ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ያስችላል ብሏል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊነት ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

አስተዳደሩ የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ እንዲሳካና የተማሪዎች ችግሮች እንዲፈቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አረጋግጠዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው በጥቂት ተማሪዎች መካከል የተከሰተው ግጭት የግለሰቦች እንጂ፤ከብሔር ጋር የሚያያይዘው ነገር እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች ለመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊነት በግንባር ቀደም ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ዛሬ  የመማር ማስተማር ሂደት ሙሉ በሙሉ መጀመሩን የኢዜአ ሪፖርተር አስተውሏል፡፡

በዩኒቨርሲቲ ውስን ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ላለፉት ሁለት ሣምንታት ትምህርት ተቋርጦ ነበር ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም