በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማሳካት ትኩረት አንዲሰጥ ተጠየቀ

77

ጋምቤላ ግንቦት 19 / 2011 በጋምቤላ ክልል በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተያዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማሳካት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

በክልሉ የእቅዱን  መካከለኛ ዘመን የስራ አፈፃፀም የሚገመግም የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዕቅዱ የተያዙትን ግቦች ለማሳካት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

በክልሉ በዕቅዱ የተያዙትን ሥራዎችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የመሰረተ ልማት ተቋማት አለመሟላት በክልሉ የፀጥታና ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች  መቃለል እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት በቀሪው ጊዜ በትኩረት መሥራት ወሳኝነት እንዳለው  ተናግረዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኩዊች ዊው  በክልሉ መንግሥት ህዝቡን አስተባብሮ የሚሰራበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የክልሉን ህዝብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚካሄው የመንደር ማሰባሰቡ መርሃ ግብር መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆኑ ልማት ስራዎች ላይ የራሱን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጎርደን ኮንግ ናቸው፡፡

በመሆኑም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በክልሉ የተያዙ የልማት ግቦችን ለማሳካት ሊታሰብበት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ኮማንደር ኡማን ኡጋላ በሰጡት አስተያየት በክልሉ የታቀዱት የልማት ስራዎችን እውን ለማድረግ የግብርናና የትምህርት ዘርፎች መጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡

በተለይም የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል የግብርና ግብዓቶችንና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ በትኩረት ልንሰራ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኡቦንግ ቤል በሰጡት አስተያየት በክልሉ የተያዙ የልማት ግቦችን ለማሳካት በቀጣይ የሁሉም አካላት ቅንጅታዊ ስራ መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተለዩ ችግሮችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በተለይም በአመራሩ ዘንድ የማስፈጸም አቅምን በማጎልበትና ተጠያቂነትን በማስፈን ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል አመልዕክተዋል

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ እንዳሉት የፌደራል መንግስት በክልሉ የታቀዱ የልማት ግቦች እውን ለማሳካት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የተዘጋጀው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅቱ እያጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የተያዙ ስራዎችን ለማሳካት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ አንድነቱን በማጠናከር ለልማትና ሰላም በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም