በኢትዮጵያ መሬት ፍትሃዊና ግልጽ በሆነ መንገድ የማግኘት ከፍተኛ ችግር እንዳለ አንድ ጥናት አመለከተ

64

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011 በኢትዮጰያ ለንግድ ስራ የሚሆን መሬት ፍትሃዊና ግልጽ በሆነ መንገድ የማግኘት ከፍተኛ ችግር እንዳለ አንድ ጥናት አመለከተ።

በኢትዮጵያ በተለይም ከተሞች አካባቢ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማካሄድ የሚያስችል የቦታ አቅርቦት ችግር እንዳለ በተለያዩ ወገኖች ሲነሳ ይደመጣል።

ይህንኑ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ነው የኢትዮጰያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሲዊዲን ኢምባሲ ጋር በመተባበር ጥናት ያካሄደው።

ዛሬ ይፋ የሆነው ጥናቱ በኢትዮጰያ ለንግድ ስራ የሚውል መሬት  አቅርቦት የፖሊሲ፣ መመሪያዎችና የአሰራር ሂደትንና ችግሮቹን ለመለየት ላለፉት አራት ወራት ነው የተካሄደው።

በመላው አገሪቱ የተውጣጡ 17 ከተሞች በጥናቱ የተዳሰሱ ሲሆን በአስተዳዳራዊ ማነቆዎች፣ በተቋማት የማስፈጸም አቅም ማነስና በህግ ክፍተት የንግዱ ማህበረሰብ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መሬት እንደማያገኙ ጥናቱ አረጋግጧል።

የጥናቱ አስተባባሪና አቅራቢ አቶ ኢያሱ ኩመራ እንዳሉት መጠይቁ ከተበተነላቸው 394 ነጋዴዎች መካካል 95 በመቶ የሚሆኑ በአገሪቱ ያለው የመሬት አቅርቦት አዝጋሚና ፍትሃዊ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

ከአጠቃላይ ተጠያቂዎቹ መካከል 63 በመቶ የሚሆኑት ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከቤተሰብ ወይም በሌላ መንገድ ባገኙት በራሳቸው መሬት ላይ ነው።

በጥናቱ የተካተቱት 88 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ  መሬት ለማግኘት የብድር አቅርቦት እንዳልተመቻቸ ይናገራሉ።

በዚህም ሳቢያ ንግድ እንቅስቃሴውን በሚገባው መንገድ በማስፋፋት፤ የገበያ ተወዳዳሪነትን በመፍጠር ለአገራዊው ምጣኔ ኃብት ሊጫወት የሚችለውን ሚና በወጉ እንዳይጫወት እያደረገው መሆኑን በጥናቱ ተወስቷል።

ጥናቱ እንደጠቆመው በመሬት አድስተዳደር ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አብዛኛው የአገሪቱ ተቋማት ጠንካራ ባለመሆናቸው መሰረተ ልማት በበቂ ሁኔታ የተሟላለት መሬት ማቅረብ አልተቻለም።

በሊዝ አዋጁ ላይ የተቀመጡ መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበርና ግልጽ አለመሆን በመሬት አቅርቦት ላይ ህገ-ወጥነት እንዲስፋፋ አድርጓል ሲሉም የጥናቱ አስተባበሪ ተናግረዋል።

የከተማ ሊዝ አዋጁ መሰረት ማንኛውም ከተማ በሊዝ አዋጁ መተዳደር አለበት ቢልም ይሀ ግን  በበዙ ከተሞች እየተተገበረ አይደለም።

ለዚህም የከተሞች የአስተዳደር ወሰን አለመኖር፣በአንዳንድ ከተሞች የከተማ ምክር ቤት አለመኖር፣ የህግ አፈጻጻም ክፍተት መኖር ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ መንግስት የተቋማትን የማስፈጸም አቅም መጠናከር፣ የሊዝ አዋጁን በየሁለት ዓመት መሻሻል፣ በከተማ ከንቲባዎች በልዩ ሁኔታ የሚሰጠውን መሬት በህግ መሰረት እንዲፈጸም ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጥናቱ አስተባባሪ ገልፀዋል።

በተጨማሪ ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንካራ የሆነ ተቋምና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተጠቁሟል።

የኢትዮጰያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ አዘዘው እንዳሉት ምክር ቤቱ በግሉዘርፈና በመንግስት መካካል ምቹ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ይሰራል።

መንግሰትም የግሉ ዘርፍ በግልጽነት ላይ የተመሰረተ ውጤታማ የሆነ የመሬት አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆን ያግዛል።

ነገር ግን የንግዱ ማህበረሰብ ተገቢ በሆነ መንገድ የመሬት አቅርቦት እያገኘ እንዳልሆነ የዘርፉም እድገት ማነቆ መሆኑ ተለይቷል ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የሆነው ጥናት ይህን ችግር ለመፍታት ዓላማ አደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ የፖሊሲና የአሰራር ማነቆዎች መፍትሄ እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል።

በመድረኩም የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ፖሊሲ አውጭዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም