በፍቼ ከተማ የተገነባው ዘመናዊ የሰላሌ ኦሮሞ ባህል ማዕከል ተመረቀ

135

ግንቦት 18/201 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ በህዝብ ተሳትፎ የተገነባው ዘመናዊ የሰላሌ ኦሮሞ ባህል ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተመረቀ።
በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ለእኩልነት፣ ለነፃናትና ለትምህርት ተደራሽነት በፅኑ በመታገል በህዝቡ በጀግንነት ለሚታወቁት ብርጋዴር ጀነራል ታደሰ ብሩ መታሰቢያ በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰራው ኃውልትም ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርቋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእዚህ ወቅት ጄነራል ታደሰ ብሩ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ብሎም ለኦሮሞ ህዝብ ፍትህና ነጻነት የታገሉ ጀግና መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዲሱ ትውልድ የእርሳቸውን አርአያነት በመከተል የራሱን ታሪክ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው፣ በተለይ ትምህርትና እውቀቱን በማስፋት ለሀገራዊ አንድነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሀብቶም በቀለ በማዕከሉ ምረቃ ላይ እንደተናገሩት ለማዕከሉ ግንባታ በዞኑ 13 ወረዳ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከዞኑ ውጪ የሚኖሩ ተወላጆች አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ህብረተሰቡ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የማዕከሉን የግንባታ ወጪ በገንዘብ፣ በዕውቀትና በቁሳቁስ መሸፈናቸውንም አስረድተዋል።

እንደአስተባባሪው ገለጻ የክልሉ መንግስት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ለማዕከሉ መጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል።

ግንባታው በ2005 ዓ.ም ተጀምሮ ዛሬ ለምረቃ የበቃው የሰላሌ ባህል ማዕከል 91ነጥን 5 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።

ማዕከሉ 3 ሺህ ካሬ ሜትር በሚጠጋ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን 2ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አለው።

በተጨማሪም እያንዳንዳቸው ከ300 እስከ 400 ሰዎች የሚያስተናግዱ ስድስት አነስተኛ አዳራሾችና አንድ የባህል ሙዚየም አካቶ መያዙን አስተባባሪው ተናግረዋል።

አነስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾቹ  በጀግንነታቸውና በፅናታቸው በሚታወቁት አቡነ ጴጥሮስ (መገርሳ በዳሳ)፣ እንዲሁም ሻለቃ አበበ ቢቂላ፣ በሌላ በኩል  የአካባቢው አርአያ  ለሆኑት ኃይለማሪያም ገመዳ ፣ አገሪ ቱሉ ፣ ወሰኑ ዲዶ እና አብቹ በየነ የተሰየሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማዕከሉ የሲኒማ፣ የአስተዳደር ቢሮዎችና ካፍቴሪያን ጨምሮ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች እንዳሉትም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዕከሉን ከመረቁ በኋላ ከዞኑ 13 ወረዳዎች ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያዩ ሲሆን በከተማው የልማት ስራዎችንም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም