ከተማ አቀፍ የስፖርት ፌስቲቫል ተካሄደ

42

አዲስ አበባ ግንቦት  18/2011 አንድነትን ማጠናከር ዓላማ ያደረገ ከተማ አቀፍ የስፖርት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሄደ።

በፌስቲቫሉ ላይ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ታዳጊ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና በእድሜ የገፉ አረጋዊያን በፌትቫሉ ላይ የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የኤሮቢክስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል።

ከባህላዊ ስፖርቶች መካከልም የፈረስ ጉግስ የቀረበ ሲሆን ከዘመናዊ ደግሞ የመኪና፣ የብስክሌትና የመሳሰሉ ስፖርታዊ ክንዋኔዎች መርሃ ግብሩን አድምቀውታል።

የአካል ጉዳተኞች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ የውሹ፣ ቴኳንዶና የእጅኳስም እንደዚሁ ከማለዳው ጀምሮ ተካሂዷል።

የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጤናቸውን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ለአንድነት ጸር የሆነውን ዘረኝነት መከላከል ላይ እንዲያተኩሩም ጥሪ ቀርቧል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴው ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራል።

ምክትል ከንቲባው ባለዕድል ለሆኑ የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች የብስክሌት ሽልማት ሰጥተዋል።

በዚሁ መሰረት 95 ብስክሌቶች በኩፖን ለደረሳቸው ባለእድለኞች ተከፋፍለዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ በሺዎች የሚገመቱ ተሳታፊዎች ከማለዳው ጀምሮ በመገኘት ልዩ ልዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም