በኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪኮችና እሴቶች ላይ የሚያጠነጥነው 'ድርና ማግ' መጽሃፍ ተመረቀ

71

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011በኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪኮችና እሴቶች ላይ የሚያጠነጥን 'ድርና ማግ' የተሰኘው መጽሃፍ ዛሬ ተመረቀ፡፡
'ድርና ማግ የመጣንበት መንገድ፣ ስጋትና ተስፋችን' በሚል ርዕስ በአቶ ብሩክ ከድር የተጻፈው መጽሐፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ በሚገኘው የኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ዛሬ ማምሻውን ተመርቋል።

በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የታደሙትን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።

በ320 ገጾች የተቀነበበው 'ድርና ማግ' በኢትጵያውያን የጋራ ታሪክና እሴቶች ላይ ያጠነጠነ ሲሆን የታሪክ አጻጻፍ፣ የመጣንበት መንገድ፣ ተስፋና ስጋቶች በሚል በተለያየ ጠርዞች የሚገኙ ትርክቶችን ይተነትናል።

አገር ምስረታ፣ በታሪክ መንገዶች የተወረሱ ጥያቄዎች፣ የብሄርና ዜግነት ማንነት ፖለቲካ፣ የባህልና ኢኮኖሚ የጋራ እሴቶች ያጋጠሙ ስጋቶችና መውጫ መንገዶችንም ይዳስሳል።

በ5 ምዕራፎች የተከፈለው መፅሃፍ እንደ ድርና ማግ የተሳሰረና የአብሮነት ታሪኩ ጥልቅ መሰረት ያለው ለማሳየ መሆኑን ደራሲው ገልጿል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መጽሃፉ ለአካዳሚክ ምርምር ለማድረግ ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር፣ ለፖለቲካ ተዋናዮች ሚዛናዊና ምክንያታዊ ሃሳብ እንዲኖራቸው ትንተናዎችን የጎላ ሚና እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል።

መጽሃፉ ቀደምት መሪዎች በጊዜው ነባራዊ ሁኔታ ጊዜውና አዕምሯቸው በፈቀደው መጠን አገር ሲመሰርቱ በፈጠሩት ስህተታቸው ተምረው ጠንካራውን ነገር መውረስ ላይ ደካማ መሆናችንን በግልጽ የሚያሳይ መጽሃፍ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ በርካታ ዘመን ታሪካዊ አመጣጥ ወገንተኝነት ይታይበታል የሚለው ጥያቄ ባለፉት 27 ዓመታት የቆየ ብዝሃነትን ጥያቄ ቢመልስም፣ በጋራ እሴቶች፣ ማንነትና አንድነት ላይ ግን በሚገባ አልተሰራም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህራን የሆኑት ዶክተር ከይረዲን ተዘራ በመጽሃፉ ላይ የራሳቸውን ሃሳብ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እንደ ድርና ማግ የተሳሰረ ማንነትን ከቋንቋ፣ ባህልና ኢኮኖሚያ ትስስሮች እንደ ድርና ማግ የተሳሰረው የአገራዊ እሴቶች ተጠብቀው መቆየታቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ ማንነቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ማንነቶች ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩት ግን በበርካታ ዘመናት እንደ ድርና ማግ የተሳሰረ መሰረት ያለው የጋራ ማንነትና ታሪክ በመኖሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የጋራ ታሪኮችና እሴቶች ማጉላት፣አንድነት ላይ ማጠናከር፣ ጠርዝ ለጠርዝ የሚጠቋቆሙ ሊሂቃንን ማቀራረብ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት በጋራ ታሪክና እሴቶች ላይ አበክረው መስራት እንዳለባቸው ተጠቁማል።

በዚህም ከትናንት በመማር ነገን በመገንባት አገሪቱ ከገባችበት የህልውና ችግር የመውጫ መንገዶችም ተጠቅሰዋል።

ድርና ማግ፤ የመጣንበት መንገድ፣ ስጋትና ተስፋችን መጽሃፍ በ100 ብር ገበያ ላይ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም