የወጣቶች ራሳቸውን በጥልቀት እያወቁ መምጣት አገርን ለመረከብ ወሳኝ ነው - ወይዘሮ ሙፈሪያት

44

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011የወጣቶች ራሳቸውን በጥልቀት እያወቁ መምጣት አገርን ለመረከብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ። 

የአፍሪካ ቀን ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) አዳራሽ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በተገኙበት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት እንደገለጹት፤ ወጣቶች ዛሬያቸውን በመስራት ነገን በማሰብ የአህጉርና የአገር ተረካቢ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

አህጉርም ሆነ አገር ተረካቢ መሆን የሚቻለው በመጀመሪያ ራስን በማወቅ እንደሆነ ገልጸው፤ ወጣቱ ትውልድ ራሱን፣ ማህበረሰቡንና አገሩን በጥልቀት ለማወቅና ለመረዳት መጣር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

''ራስን ማወቅ ምርጥ አርቲስት፣ ነጋዴ፣ ሳይንቲስት፣ ፖለቲከኛ፣ ወዘተ ለመሆን ያስችላል'' ብለዋል።

በተሰማሩበት መስክ ጥልቅ ዕውቀት ማጣት አገርን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት ወጣቶች ከዚህ ትምህርት ወስደው ራሳቸውን ለማብቃት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዕውቀትና ጊዜን ሳይሰስቱ ከወጣቱ ጋር መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የወጣቱን ችግር ለመፍታት አዲስ ፕሮጀክት ተቀርጾ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በማማከል ወደስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም