በኢትዮጵያ የሰብል ምርታማነት አሁን ካለው አቅም አኳያ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

144

አዲሰ አበባ ግንቦት 17/2011በኢትዮጵያ የሰብል ምርታማነት አሁን ካለው አቅም አኳያ እጅግ አነስተኛ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ዛሬ በአዳማ ከተማ በተጀመረው የግብርና ልማት አመራር ንቅናቄ መድረክ ባቀረቡት ዳሰሳዊ ጥናት ስንዴ፣ በቆሎና ጤፍ በመሳሰሉት ሰብሎች የሚያበረታታ ምርታማነት የተመዘገበ ቢሆንም፤ አሁንም ከምርምር ከሞዴል አርሶ አደሮችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው "ምርታማነት ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በምርምር የተረጋገጠው የምርት መጠን በሄክታር 100 ኩንታል መሆኑን አመልክተው፤ በሞዴል አርሶ አደር ላይ በተካሄደ የእርሻ ስራ ደግሞ እስከ 65 ኩንታል የስንዴ ምርት የማግኘት አቅም እንዳለ መረጋገጡንም ገልጸዋል።

ሆኖም ከአገሪቷ በአጠቃላይ ሁኔታ ከአንድ ሄክታር እየተሰበሰበ ያለው የስንዴ ምርት ከ39 ኩንታል አይበልጥም።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ አስፈላጊው ርብርብ ተደርጎ በሞዴል አርሶ አደር ደረጃ የተገኘውን ያህል ኩንታል ስንዴ ከተመረተ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ይቻላል።

በመላው አገሪቷ የሞዴል አርሶ አደሩን ተሞክሮ ስራ ላይ በማዋል በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ተጨማሪ የስንዴ ምርት መሰብሰብ እንደሚቻልም አመልክተዋል።

በመጪዎቹ ዓመታት ትኩረት ከሚሰጣቸው ዘርፎች መካከል የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት እንደሆነም ገልጸዋል።

ሌላኛው ጽሁፍ አቅራቢ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርአት ማስተባባሪያ ማዕከል ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ብናልፍ እንዷለም በበኩላቸው፤ የግብርናው ልማት በተለይ የመጪው የመኸር ወቅት ቁልፍ አገራዊ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የግብርና ዘርፉ አገሪቷ ከገጠሟት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፈተናዎች ለማላቀቅ የሚያስችል መሆኑን አመልክተው፤ መንግስት በተለይም የክረምት የግብርና ስራውን ቅድሚያ ትኩረት እንደሰጠውም ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ በግብርና ልማት የመጪውን ክረምት የእርሻ ስራ በቅርበት የሚመራ ብሔራዊ ግብረ ሃይል መቋቋሙንም አስረድተዋል።

ተመሳሳይ አላማ ያላቸው ግብረ ሃይሎች ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ እንደሚዋቀር ገልጸው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የግብርናውን ስራ ሙያዊ ተግባራት የሚከታተልና ድጋፍ የሚሰጥ የቴክኒክ ኮሚቴ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን እንደሚዋቀር ነው ያረጋገጡት።

የውሃ መስኖና ኢኒርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የግብርና ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን አስተማማኝ ማድረግ ይገባል። ለዚህም በመጪው ክረምት ችግኞች ይተከላሉ።

በዛሬው የንቅናቄ መድረክ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስር አቶ ደመቀ መኮንን እንደገለጹት፤ የግብርናው ዘርፍ ተስፋ የሚሰጡ ተሞክሮዎች የተመዘገቡበት ነው። ሆኖም ተሞክሮዎቹን ወደ ሌሎች ማስፋት ባለመቻሉ ዘርፉ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ተስኖታል።

ይህ ጀምሮ የመተው ባህሪይ የሚታየበት አሰራር ወደፊት እንደማያስኬድ ያመለከቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዚህ ዓይነቱ አመለካከከትና ቁርጠኝነት መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም ከአርሶ አደሩ ጎን ሆነው በቅርበት ለሚሰሩት የልማት ጣቢያ ሰራተኞችና ባለሙያዎች ልዩ ትኩረት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህ ሲሆን ነው "የአርሶ አደሩን ማሳና ቤተሰብ እየተከታተሉ ለውጤት ማብቃት የሚቻለው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአዳማ ከተማ የተጀመረው የግብርና ልማት አመራር ንቅናቄ መድረክ ነገም የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም