ወላይታ ድቻ የፋሲል ከተማ አቻውን አሸነፈ

50

ሶዶ ግንቦት 17/2011 በ26ኛዉ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በሜዳው የፋሲል ከተማ አቻውን አስተናግዶ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸነፈ ፡፡
ባለሜዳው ድቻ ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለማምለጥ እና ፋሲል ከተማ ደግሞ ለዋንጫ የሚያደርገውን ግስጋሴ ለማጠናከር ጨዋታው እንዲጠበቅ አድርጎ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ሶስቱ የጉግሳ ልጆች ማለትም ቸርነትና አንተነህ በወላይታ ድቻ በኩል እንዲሁም ሺመክት በፋሲል በኩል በተቃራኒው የሚያደርጉት ጨዋታ መሆኑ ለጨዋታው  ተጨማሪ ድባብና ድምቀት የሰጠ ነበር፡፡

በዛሬ ውድድር ለወላይታ ድቻ የመጀመሪያውን ግብ የጨዋታ መጀመሪያው ፊሽካ እንደተሰማ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ክስተት የተለጋውን ኳስ  በአስር ቁጥሩ  ባዬ ገዛኸኝ በጭንቅላቱ ገጭቶ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ለፋሲል ከተማ ደግሞ የድቻን ተከላካዮችና የግብ ጠባቂ አለመናበብ ተጠቅሞ በ14ኛ ደቂቃ ላይ የአቻነቷን ግብ ያስቆጠረው 32 ቁጥሩ ኢዙ አዛኪ ነው፡፡

ባለሜዳው ድቻ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ  ጫና ፈጥሮ ለመጫወት የሞከረ ቢሆንም ቀሪዎችን ደቂቃዎች በመከላከል፣ በማደራጀት፣ የመሃል ክፍል ብልጫ በመውሰድና የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ከእንግዳው ክለብ ፋሲል ከተማ የተሻለ ሆኖ ነበር፡፡

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመነሻው ጀምሮ በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል በፈጣን የኳስ ፍሰትና የግብ ሙከራዎች የታጀበ ሆኖ ቆይቷል።

የጨዋታው እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ በመሆኑ ብልጫ ለመውሰድ ሲባል ቶሎ ቶሎ ተጨዋች የመቀየር አዝማሚያዎች የተስተዋሉበት ነበር፡፡

በተደረጉ የተጨዋች መቀያየር  የተሻለ አጋጣሚ መፍጠር የቻለው ወላይታ ድቻ አሸናፊ ያደረጋቸውን ግብ ያስቆጠሩት ተቀይረው በገቡት ጸጋዬ አበራና ኃይሌ እሸቱ አማካይነት በ75ኛ ደቂቃ ላይ ነው፡፡

የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በነበረው የውጤት ፍላጎት በውጥረት የተሞላና አስቸጋሪ ጨዋታ ቢሆንም በማሸነፋቸው መደሰታቸውን  ተናግረዋል፡፡

በቡድናቸው የሚስተዋለውን የተከላካይ ክፍል ድክመት ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ ለተነሳላቸው ጥያቄም ትክክል መሆኑን አምነው የተሻለ ልምድና ክህሎት ለማምጣት ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን አመልክተዋል።

የፋሲል አቻቸው ውበቱ አባቴ በበኩላቸው አሸንፈው ወይም ነጥብ ተጋርተው  ለመውጣት ቢያስቡም  ከሜዳው  አለመመቻቸት እንዳልተሳካለቸውና መቀበል ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ተጋጣሚያቸው በተጨዋች ቅያሬ በኩል በፈጠረው ጫና መብለጡን አመልክተው መሸነፋቸው  በቀጣይ ያሉባቸውን ውድድሮች በመርታት የዋንጫ አሸናፊ ከመሆን እንደሚያግዳቸው አስረድተዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሩት በዚሁ ጨዋታ ብዛት ያላቸው እግር ኳስ አፍቃሪዎች በሜዳው ተገኝተው ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ ሁኔታ ቡድናቸውን አበረታትተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም