የክልሉ የጤና አገልግሎት እንዲሻሻሉና ጥቅማ ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩላቸው የጤና ባለሙያዎች ጠየቁ

56

አሶሳ/ደብረ ብርሃን ግንቦት 17 / 2011 የቤኒንሻጉል ጉሙዝ ክልል የጤና አገልግሎት እንዲሻሻልና ጥቅማ ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩላቸው የጤና ባለሙያዎች ጠየቁ፡፡

በተመሳሳይ የደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ባለሙያዎች የሕክምና ግብአቶች እንዲሟሉላቸውና መብታቸው እንዲከበርላቸው ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።

ባለሙያዎቹ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡት ዛሬከክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች ጋር በዘርፉ በሚታዩ ችግሮች ላይ በአሶሳ ከተማ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

የአሶሳ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ባለሙያ አቶ ጌትዬ መለስ ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ሆስፒታል የተገልጋዮች ቁጥር ቢጨምርም፤ የሕክምና ቁሳቁስ አለመሟላት ችግር ሆኖ ቀጥሏል ይላሉ፡፡ 

የሕሙማን መኝታ ክፍሎች አለመሟላት፣ የታካሚዎች አልጋ ማርጀትና በሆስፒታሉ ግቢ በክረምት ወራት አምቡላንሶች በጭቃ ተይዘው ለመንቀሳቀስ መቸገር ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ 

ለረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጡ የጤና ባለሙያዎች ምንም የአቅም ግንባታና የትምህርት ማሻሻያ እንደማያገኙ ያወሱት አስተያየት ሰጪው፣ በወረዳዎች ያለው ወጥ ያልሆነ የጥቅማ ጥቅም ና ትምህርት እድል አሰጣጥ እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

''በትንፋሽና በንክኪ በሚተላለፉ በሽታዎች የመጀመሪያ ተጠቂ ስለሆንን የሥራ ላይ ዋስትና ሊኖረን ያስፈልጋል'' ያሉት የባምባሲ ወረዳ ጤና ባለሙያ አቶ አልቀሪብ መሐመድ ናቸው።

የመንጌ ወረዳ ጤና ባለሙያ አቶ መብሩክ መሐመድ በበኩላቸው በክልሉ የሚገነቡ ጤና ተቋማት የጥራት ችግር እንደሚታይባቸው ይናገራሉ፡፡

አምቡላንስ የሌላቸው ጤና ጣቢያዎች እንዳሉ የሚናገሩት እኚሁ ባለሙያ፣በከፍተኛ ወጪ የተገዙ የሕክምና ቁሳቁስ ያለ አገልግሎት በመቀመጥ ለብልሽት እየተዳረጉ ነው'' ብለዋል፡፡

አቶመላኩ ወሊሶ የተባሉ የዳንጉር ወረዳ ጤና ባለሙያ በጀት ተመድቦላቸው ቅጥር የማይፈጽሙ ወረዳዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የሕመም ማስታገሻ የሌላቸው አንዳንድ ጤና ተቋማት እንዳሉ የሚናገሩት ደግሞ መሳይ ጥሩዬ የተባሉ የሆሞሻ ጤና ጣቢያ ሠራተኛ  ሲሆኑ ፣በተለይም ጀማሪ ጤና ተቋማት በቀዶ ጥገና ባለሙያ፣ በመድኃኒትበሌሎች ግብዓቶች ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በባለሙያዎች የተነሱ አብዛኛዎቹ ችግሮች ቢሮው በግምገማ እንደለያቸው ይናገራሉ፡፡

በተለይ  የሕግና መመሪያዎች አለመተግበርና ኪራይ ሰብሳቢነት በዋነኝነት የሚታዩ ችግሮች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

ቢሮው ችግሮቹን ለመፍታት በክልሉና በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ የሚፈቱትን በጥናት ለይቶ  በአጭርና በረጅም ጊዜ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጤና ተቋማትና ባለሙያዎችም ድርሻቸውን መውሰድ እንዳለባቸውም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን የክልሉ ጤና ባለሙያዎች መሠረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች ለሚሰጡት አገልግሎት አክብሮት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በተለይ የጤና ተቋማት ሕክምና ግብዓቶችና የባለሙያዎች ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ክልላዊና አገራዊ አቅጣጫዎችን መሠረት በማድረግ ምላሸ እንደሚሰጥበት ቃል ገብተዋል፡፡

የወረዳና የዞን አመራሮች ለችግሮቹ አቅማቸው በፈቀደ መፍትሄ እንዲሰጡም ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል፡፡

የአሶሳ ሆስፒታል ግንባታ ማስፋፊያና ማሟላት ጉዳይ በ2012 ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ ሆስፒታሎችን ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በማስተሳሰር ችግሮችን ለመፍታት መታቀዱንም አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የደብረ ብርሃን ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች የሕክምና መሳሪያዎች መድኃኒት ተሟልተዉ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲመቻችና መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው የጠየቁበትን ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ አድርገዋል።

ባለሙያዎቹ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል በ2003 ጀምሮ የተተገበረዉ የፈረቃ ሥራ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲስተካከል፣ በሌሊት ፈረቃ የሚሰሩ ሐኪሞች የትራንስፖርት አገልግሎት አለመመቻቸት እንዲስተካከል ፣በተለይም ሴቶች ለሌቦችና ለደፋሪዎች የሚጋለጡበት ሁኔታ እንዲታሰብበትና የደሞዝ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚሉ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም