ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣ የተበከለ ፍሳሽ በሰዎችና እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተጠቆመ

89

ግንቦት 17/2011 ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣ ፍሳሽ በሰዎችና እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ በአዲስ አበባ ዙሪያና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ጠየቁ። 

አርሶ አደሮቹ በአካባቢያቸው የሚገኙ ወንዞች ከኢንዱስትሪ በሚለቀቅ ፍሳሽ በከፍተኛ ደረጃ እየተበከለ መሆኑን አመልክተው፤ በአካባቢው የውሃ አማራጭ ባለመኖሩ ምክንያት ብቻ ወንዙን እየተጠቀሙት መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያና በኦሮሚያ ክልል በሰበታ፣ ዱከምና ሞጆ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የሚወጣው የተበከለ ፍሳሽ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነው በስፍራው ተዘዋውሮ ለጎበኘ የጋዜጠኛ ቡድን የተገለጸው።

ይሁን እንጂ ወንዙ በኬሚካል በመበከሉ ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጡ መሆኑን አመልክተዋል።

ከወንዞቹ በሚጠቀሙት ውሃ ምክንያት በእንስሳት ላይም የፀጉር መመለጥ፣ መክሳትና እርጉዝ የሆኑት ላይ ውርጃ እያጋጠማቸው ነው የተባለው።

ሌሊት ሌሊት አያስተኛንም የተለያዬ በሽታ ላይ እየወደቅን ነው፤ ከብቶቻችንም የሚጠጡት ይሄንኑ ነው በሽታ ላይ እየወደቁ እንደሆነ ወይዘሮ ልኬ እሸቱ ተናግረዋል

ከብቶች ላይ በጣም ችግር እያስከተለ ነው መንግስት መፍቴህ ሊሰጠን ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ክብሩ ጸጋዬ ናቸው፡፡

ወይዘሮ ሞቱ መርዳሴ  "ልጆቻችንም ሆነ እኛም ጉዳት ላይ ስላለን ይሄንን አይቶ እንዲያስተካክልልን ነው እኛ መንግስትን የምንጠይቀው " ብለዋል

እነዚህ በአዲስ አበባ ዙሪያና በሞጆ አካባቢ የሚገኙ የተበከሉ ወንዞች መዳረሻቸው አዋሽ ወንዝ መሆኑ ደግሞ ችግሩን አስከፊ ያደርገዋል።

በቦታው ኢዜአ ያነጋገረው ወጣት አርሶ አደር እንደሚለው ምርቱ ለተለያዩ ነጋዴዎች የሚከፋፈል ሲሆን፤ አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞችም ይህንኑ ምርት ይጠቀማሉ።

በነዚሁ ወንዞች ብክለት መንስኤና የብክለት ደረጃቸው ላይ ምርምር የደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ሳይንስ ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ስዩም ሌታ እንደሚገልጹት፤ ወንዞቹ የዓለም የጤና ድርጅት ለመስኖ ለመጠቀም ካወጣው መስፈርት ፍፁም የማይገናኙና ከጥቅም ውጭ የሆኑ ናቸው።

ይሁን እንጂ ገበሬው አማራጭ ስለሌለው ፍራፍሬ እያመረተ መሆኑ አመልክተው፤ ምርቱ በውስጡ መርዛማ ንጥረ ነገር እንደያዘ በጥናት መረጋገጡን ነው ያብራሩት።


የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንን አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የአካባቢ ብክለት ቁጥጥርና ክትትል ህግ ተባባሪነት ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ በፍቃዱ ለችግሩ መባባስ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የቅንጅት ማነስ አንዱ ምክንያት መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ባለስልጣኑ ለባለ ሃብቶቹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ከመስጠት ባለፈ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ስንታየሁ፤ በቀጣይም የብክለት መጠናቸውን በማያስተካክሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ "ህጋዊ የእርምት አርምጃው ይቀጥላል" በማለት ተናግረዋል።

በጉብኙቱ ወቅት ቅሬታ የቀረበበት የሱፐር ደብል ቲ የሮቶና የቀለም ፋብሪካን ኃላፊዎችን በማነጋገር ስለጉዳዩ ያላቸውን ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም