በሰሜን ሸዋ አሲዳማ መሬትን በማከም ምርታማነትን ማሳደግ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ሆነ

86

ፍቼ ግንቦት 17/2ዐ11 አሲዳማ የእርሻ መሬትን በሣይንሳዊ ዘዴ በማከም ምርታማነታቸውን ለማሣደግ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮችና የፍቼ አፈር ምርምር ላብራቶር ማዕከል አስታወቀ

በዞኑ አምስት ወረዳዎች ለሶስት ዓመታት በተካሄደው ሙከራ ከዚህ ቀደም ምርት በማይሰጥ አሲዳማ የእርሻ መሬት ላይ ኖራ አፈር በመጨመር ስንዴ፣ ገብስና በቆሎ ማልማት ተችሏል።

አርሶ አደር ቶልቻ አበራ በጅዳ ወረዳ የስርጢ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ መሬታቸው አሲዳማ በመሆኑ የከብት መኖ እንኳን ሳይበቅልበት ለረጅም ዓመታት በሴፍትኔት ኘሮግራም ታቅፈው እንደቆዩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።


ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በባለሙያዎች ምክር ታግዘው አንድ ሄክታር ተኩል በሚሆነው መሬታቸው ላይ የኖራ አፈር እንዲሁም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጨመር በተለይ ባለፈው የበልግ ወቅት ስንዴና ገብስ ማምረት ችለዋል።


በእርሻ መሬት ላይ የኖራ አፈር ከሌሎች ብስባሾች ጋር መጨመር የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ሌሎችም  የአካባቢው አርሶ አደሮች እንደተከተሏቸው ተናግረዋል።


በዚሁ ወረዳ የጡማኖ ገበሬ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ነጂብ ሀምዛ በበኩላቸው ሁለት ሄክታር አሲዳማ መሬታቸው ኖራ በመነስነስ ምርታማ ማድረግ እንደሚቻል ከሌሎች አርሶ አደሮች ልምድ ቢያገኙም  የኖራ እጥረት   ችግር እንደሆነባቸው ገልፀዋል፡፡


የኖራ አቅርቦት ቢኖራቸው ለከብት መኖ ብቻ ያዋሉትን መሬታቸውን ስንዴ፣ ገብስ ና በቆሎ ዘርተው ለመጠቀም ፍላጐቱ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡


በአሲዳማ መሬታቸው ላይ ብዙም የግብርና ሥራ የማይፈልገውን "ሲናር" የተባለውን የከብት መኖ ብቻ አልምተው በዝቅተኛ ዋጋ ያቀርቡ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ በውጫሌ ወረዳ የቡሎ ቀበሌ አርሶ አደር ጉተማ ጉርሙ ናቸው።

ባለሙያዎች በሰጧቸው ድጋፍ በባለፈው የመኸር ወቅት ሃያ አራት ኩንታል ስንዴ ለማምረት እንደቻሉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ማሣቸውን በኖራና በተፈጥሮ ማዳበሪያ በማከም ገቢያቸውን ለማሳደግና ሕይወታቸውን ለመቀየር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

ዘንድሮ መሬታቸውን አስቀድመው በኖራና በተፈጥሮ ማዳበሪያ በማለስለስና   የተሻሻሉ አሰራሮችን በማሣቸው ላይ በመተግበር ጥሩ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አርሶ አደሩ አመልክተዋል፡፡


የፍቼ አፈር ምርምር ላብራቶር ማዕከል ኃላፊ አቶ ዳዲ ቦያዓ በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ላብራቶሪው በሰሜን ሸዋ በተመረጡ አምስት ወረዳዎች አሲዳማ መሬትን ለማልማት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በወረዳዎቹ 89 ቀበሌዎች በሰርቶ ማሣያ ጣቢያዎችና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ አሲዳማ መሬትን ምርታማነት ለማሣደግ ያደረጉት ሣይንሣዊ ጥረት ውጤት ማስገኘት ችለዋል፡፡

በመቶ ዘጠና ሄክታር መሬት ላይ ባደረጉት እንቅስቃሴ እንደ ወረዳው የአፈር ፀባይ በሄክታር ከሁለት ኩንታል በላይ ምርት ለመስጠት ያልቻለ አሲዳማ የእርሻ መሬት በኖራ በማከም  እስከ አስራ አምስት ኩንታል ስንዴ ፣ገብስና በቆሎ ማግኘት መቻሉን የማዕከሉ ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡


በሰርቶ ማሣያ ደረጃ ሲካሄድ  የቆየውን የሙከራ ምርምርበአሁኑ ወቅት ወደ አርሶ አደሮች ማሣ በማስፋፋት ከአስር ሺህ በላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች ገብስ ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ ማምረት እንዲጀምሩ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ማዕከሉ በተጨማሪም በዞኑ 13 ወረዳዎች በ11 የአፈርናየውሃ ናሙናዎች ላይ ምርምር በማካሄድ የማዳበሪያ አጠቃቀምና የተስማሚነት ሁኔታን በመለየት ለአርሶ አደሮች ምርታማነት እየሰራ ነው።

ኃላፊው እንዳሉት የተፈጥሮ የማዳበሪያ አጠቃቀምን ለማሻሻል አርሶ አደሩ የአፈር ናሙናዎችን እያስመረመረ የእርሻ መሬቱ የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ ዓይነት መርጦ እንዲጠቀም የማስተዋወቅና የማስፋፋት የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል፡፡

በዞኑ 8ሺ ሄክታር አሲዳማ አፈር መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች  ኖራ በማቅረብ  ቴክኖሎጂውን በስፋት ለመጠቀም የጥናትና የመለየት ሥራ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ በዞኑ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት የግብአትና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ከበደ ናቸው።


በመጪው የመኸር ወቅት 3ሺ200 ሄክታር አሲዳማ ለማልማት የኖራ አፈር መቅረቡን ተናግረዋል፡፡


በዞኑ 13 ወረዳዎች ስድስት መቶ ሺህ ሄክታር መሬት በመጪውየመኸር ወቅት በሰብል ዘር ለማልማት  ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም