የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የግንቦት 20ን የድል በአል የጽዳት ዘመቻ በማካሄድ አከበሩ

60
ጅማ ግንቦት 30/2010 የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የግንቦት 20ን የድል በአል ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን ጋር በማስተሳሰር በጅማ ከተማ የፅዳት ዘመቻ በማካሔድ አከበሩት። የጅማ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ እንደገለፁት የዘንድሮው የግንቦት 20 ቀን የድል በዓል ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን ጋር በማስተሳሰር የጅማ ከተማን ፅዱና ለኑሮ አመቺ ለማድረግ በሚጠቅም መልኩ በፅዳት ዘመቻ አክብረዋል። ''የግንቦት 20 የድል በአል የብሄር ብሄረሰብ፣ የጾታና የሃይማኖት እኩልነትን የተረጋገጠበት ነው'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በቆይታቸው ልዩነታቸውን ውበታቸው አድርገው እንዲገነዘቡና ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገር ግንባታ የሚጠቅም ስብዕና ተላብሰው እንዲወጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። የግንቦት 20 የድል በዓል “ከፕላስቲክ የፀዳ አካባቢ እንፍጠር!” በሚል መርህ ዘንድሮ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን በዓል ጋር በማስተሳሰር በፅዳት ዘመቻ ሲከበር የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳትፈዋል ። በጽዳት ዘመቻው ከተሳተፉት መካከል በዩኒቨርሲቲው የግብርናና እንስሳት ኮሌጅ የአስተዳደር ሰራተኛ  አቶ  ስለሺ ዳምጠው በሰጡት አስተያየት “በበዓሉ ምክንያት ያከናወንነው ስራ ለጅማ ከተማ ፅዳት ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር አብሮነታችንና ፍቅራችንን ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ ነው'' ብለዋል። ከዩኒቨርሲቲው ዋናው ጊቢ በጽዳት ዘመቻው የተሳተፉት ወይዘሮ እናትነሽ ወርቁ በበኩላቸው የግንቦት 20 የድል በአል ምክንያት በማድረግ በከተማ ጽዳት መሳተፋቸው በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መካከል ጤናማ ግንኝነት እንዲጎለብት ያግዛል ሲሉ ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም