የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሄደዋል

58

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመከላከያ ያደረጉት ጨዋታ 26 ለ 26 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 22 ከፍ በማድረግ በነበረበት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ በ13 ነጥብ እዛው የነበረበት አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን 28 ለ 26 አሸንፏል።

መቐለ ሰብዓ እንደርታ ነጥቡን ወደ 20 ከፍ በማድረግ በነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በሰባት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።

የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ነገ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል።

ፕሪሚየር ሊጉን በ24 ነጥብ እየመራ የሚገኘው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የነገውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ከፍ ማድረግ ይችላል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከቀኑ ስምንት ሰአት ፌዴራል ፖሊስ ከጎንደር ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ነገ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከከምባታ ዱራሜ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ምክንያት በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ በመግለጹ ከምባታ ዱራሜ በፎርፌ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 አሸናፊ እንደሆነ ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይም ሳምንታት መርሃ ግብሮች ከድሬዳዋ ከተማ ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በውድድሩ ደንብ መሰረት የፎርፌ ውጤት እንደሚያገኙ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

ድሬዳዋ በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ ማሳወቁን ተከትሎ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሚጫወቱት የእጅ ኳስ ክለቦች ቁጥር ወደ ዘጠኝ ዝቅ ብሏል።

በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት አንድ ክለብ ሲያሸንፍ ሁለት ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን አቻ ሲወጣ አንድ ነጥብ ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም