ድጎማው ሳይንሳዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ኮሚሽን እንደሚቋቋም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ

88

መቀሌ ግንቦት 17/2011 የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ ሳይንሳዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ኮሚሽን የሚቋቋም መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

በመቀሌ ሲካሄድ የቆየው የፌዴራል፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች መድረክ በተለያዩ ጉዳዮች ከመከረ በኋላ ዛሬ አጠናቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉበኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በመድረኩ እንደገለጹት በቅርቡ የሚቋቋመው ኮሚሽኑ ከበጀት ድጎማና ቀመር ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የነበሩትን አሰራሮች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄዱ ለምክር ቤቱ ድጋፍ የሚያደርግ ነው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየዓመቱ የሚፀድቀውን በጀት ፌዴሬሽኑ ከ22 ዓመታት በላይ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ መሰረት ለክልሎች የበጀት ቀመር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም አልፎ አልፎ ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።

በቅርቡ በተካሄደው ጥናት ከበጀት ድልድል ጋር ተያይዞ ፌዴሬሽኑ ያለበትን የአቅም ክፍተት የሚሞላና ድጋፍ የሚያደርግ ኮሚሽን እንዲቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት፣ የጋራ ገቢዎችና ቋሚ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ኃይሉ ኤፋ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቅሰው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ውይይት መደረጉን አስረድተዋል።

የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ክልሎችን አሳታፊ አለመሆኑን በዙሪያው ጥናት ያደረጉት ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ዶክተር አሰፋ ፍስሃ ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ከክልልና ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ካለው የጋራ መድረክ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሎች አመራሮች እየተገናኙ የሀገሪቱን የልማት ስራዎች የሚያዩበት አሰራር አለመኖር በጥናቱ መረጋገጡን ዶክተር ፍስሃ ተናግረዋል።

“የተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብለትን አዋጅ ከማፅደቁ በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያይበትና ክልሎችም በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ያላቸው ሃሳብ በፅሁፍ የሚያቀርቡበት መንገድ ቢመቻች አሳታፊነቱን የሚያጎለብት ነው “ብለዋል።

ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ በህገመንግስቱ አንቀፅ 3 የተቀመጠው የዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስና ሌሎች መብቶች በተሟላ መልኩ የሚተገበሩበትና የሌሎች ክልሎች ተወላጆች መብቶች የሚያስከብሩበት አዋጅ ሊኖር እንደሚገባም የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ክልሎችን በማይጋፋ መልኩ ዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ ህገመንግስታዊ መብታቸውን እንዲያስከብሩ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም