የፍቼ ጨምበላላ በዓል በአዲስ አበባ ተከበረ

229

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011 የሲዳማ ፍቼ ጨምበላላ በዓል የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሲዳማ ተወላጆች በተገኙበት በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ተከበረ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ መኖሪያ በሆነቸው አዲስ አበባ የሲዳማን ህዝብ የሚመጥን ታሪክ የሚያንጸባርቅ ስራ እንደሚሰራ በዚሁ ወቅት ጊዜ ገልጸዋል።

በመዲናዋ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ በመሆን ኢትዮጵያን ለማበልጸግና ለማልማት መረባረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪው ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ የፍቼ ጨምበላላ በዓልን አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች፣ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቃሬ ጫዊቾ፣ የኦሮሞ አባ ገዳዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሲዳማ ተወላጆች ተገኝተዋል።

የዘንድሮው የሲዳማ ፍቼ ጨምበላላ በዓል ግንቦት 22 እና 23 ቀን 2011 ዓ.ም በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ ይከበራል።

ፍቼ ጨምበላላ በሚል መጠሪያ የሚከበረው በዓል በሲዳማ ብሔረሰብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለው ፌስቲቫል ነው።

የፍቼ ጨምበላላ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች ከተመዘገቡ በዓላት አንዱ ነው።

የሲዳማ ሴት ከጋብቻ በኋላ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቤተሰቦቿ የምታደርገውን ጉዞ በማስታወስ የሚከበር በዓል ነው ፍቼ ጨምበላላ።

ሴቷ ወደ ቤተሰቦቿ ስታመራ በቆጮና በቅቤ የሚሰራ ቡርሳሜ የተሰኘ ባህላዊ ምግብ አዘጋጅታ መሆኑም ይነገራል።

ቡርሳሜውን ቤተሰቦቿ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን እየተመገቡ ጊዜውን በደስታ የሚያሳልፉበት ልዩ ወቅት ነው።

ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የቆየው ታሪክ የሲዳማ ህዝብ በዓመት አንድ ጊዜ የሚውለውን የፍቼ ጨምበላላ በዓል  መነሻ ተደርጎ ተመዝግቧል።

ፍቼ ጨምበላላ የሲዳማን ህዝብ አንድነትና ፍቅር የሚያንጸባርቅ መድረክ ሆኖ ለዘመናት ሲከበር የቆየ በዓል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም