የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያየ

80

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ የሚከፈልበትን በሚመለከት በቀረበው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላከ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 69ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች  ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በቅድሚያ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ  የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

በአገሪቷ የካሳ አዋጅ ተደንግጎ በስራ ላይ ከዋለ 13 ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ  ወቅታዊነት የጎደለው ሆኖ ተገኝቷል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በከተማም ሆነ በገጠር ባለ ይዞታዎች ለህዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቁ ሲደረግ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን የተነሽዎች የመብት  ድንጋጌዎች ባከበረና በመሬት ዘርፍ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚደረገውን  ርብርብ ለመደገፍና የመንግስትን ልማታዊነት ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ እንዲሆን አዋጁን አሻሽሎ ለሚንስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ማስተካከያዎችን  በመጨመር ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

ምክር ቤቱ የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል ተዘጋጅቶ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይም የተወያየ  ሲሆን፥ ነባሩ አዋጅ ዲክላራሲዮን እንዲሻሻልና እንዲሰረዝ የማይፈቅድ በመሆኑና  እንዲሁም የንግድ ስራን ከማሳለጥአንፃር በርካታ ችግሮች የነበሩበት መሆኑን በመግለፅ  የገቢዎች ሚኒስቴር የማሻሻያ አዋጁን አዘጋጅቶ አቅርቧል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በቀረበው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ላይ ተወያይቶ እንዲፀድቅ  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በአስራኤል መንግስታት መካከል በተለያዩ ዘርፎች የተፈረሙ ስምምነቶችን ለማፅደቅ በቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ እንዲፀደቁ ለህዝብ  ተወካዮች ምክር ቤት ልኳቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም