የግብርናው ዘርፍ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እንደሚቀጥል ተገለፀ

78

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011በአሁኑ ወቅት አገሪቱን ለገጠሟት ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፈተናዎች የግብርና ዘርፍ መድህን በመሆኑ የመንግስት ትኩረት ሆኖ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።


ከ1ሺ 500 በላይ የግብርና ባለሙያዎች፣ የዘርፉ አመራር እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት ‘‘ለግብርና ትራንስፎርሜሽን የአመራር  ሚና'' በሚል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የግብርና ዘርፍ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ይቀጥላል።

''ኢትዮጵያን እያሳሰቧት የመጡት የስራ አጥነት፣ የምግብ ዋስትና እጦት፣ የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሬ ቁልፍ ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን መከላከል የሚቻለው የግብርና ዘርፉን በማዘመን ነው'' ብለዋል።

ባለፉት አመታት ለተመዘገበው የአገሪቱ እድገት የግብርናው ዘርፍ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ ካለው እምቅ ሀብት አኳያ ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የምግብ ዋስትና ችግር ላይ ወድቀው በየጊዜው እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ይህንን ተከትሎ አገሪቱ ከውጭ እህል እየገዛች መሆኗን በዋናነት አንስተዋል።

ከዚህም በላይ የህዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው፣ እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ ብሎም ሀገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የማሸጋገር ተስፋ ለማለምለም የግብርናውን ዘርፍ ማሳደግ ወቅቱ የሚጠይቀው እንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ በተለይ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮችያለባቸው ሃላፊነት የላቀ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ አስገንዝበዋል።

''በተለመደው የግብርና አመራርና አሰራር መቀጠል የሚታየውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የተለየ ምልከታና ስልትን የመቀየስ ግዴታ አለባቸው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም