የልማት ስራዎች እና የሃብት አጠቃቀም በተጠያቂነት ሊፈጸም እንደሚገባ ምክር ቤቱ አሳሰበ

71

ግንቦት 17/2011 በዋግ ኅምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የልማት ስራዎች እና የሃብት አጠቃቀም ላይ ተጠያቂነት ባለው አካሄድ ሊፈጸም እንደሚገባ የአስተዳደሩ ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ከግንቦት 15/2011ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሰቆጣ ከተማ ባካሄደው 18 መደበኛ ጉባኤው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሟል፡፡

የአስተዳደሩ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኃይሉ ሚሰው በጉባኤው እንዳሉት በሴፍትኔት የታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ማሻሻያና ሃብት ማፍራት የሚችሉበትን ስርዓት በአግባቡ ሊፈጸም ይገባል፡፡

በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን ማር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በክልሉ መንግስት ወጪ የተደረገባቸው 4 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በአጭር ጊዜ ለገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ መመቻቸት እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡

ተፋሰስን መሰረት በማድረግ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በአግባባቡ ተከልለው እና ተጠብቀው የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎችና የምክር ቤት አባላት ድጋፍና ክትትል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ደግሞ በተከዜ ሃይቅ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የዓሳ ማጥመጃ መረብና አስጋሪዎችን ለመከላከል ህጋዊ አሰራር መዘርጋትም ያስፈልጋል ብለዋል።

የነፍሰጡር እናቶች መቆያ ማዕከል የሌላቸውን የጤና ተቋማት እንደሟላላቸው አመልክተዋል።

የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ግብዓትና የተሻሻሉ አስራሮች ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ በወቅቱ እንዲቀርብም ዋና አፈ ጉባኤው ጠቁመዋል፡፡

በአስተዳደሩ የሚከናወኑ አነስተኛ ግድቦች ፣የትምህርት ተቋማትና ለሌሎችም የልማት ስራዎች  ወጪ የሚሆኑ የህዝብና የመንግስት ሀብቶች አጠቃቀምና አያያዝ ተጠያቂነት ባለው መልኩ ሊፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምክር ቤቱምየአስተዳደሩን  የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጦ በመገምገም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አመላክቷል።

ጉባኤው ትላንት ከመጠናቀቁ በፊት የስራ ኃላፊዎችን ሹመት ያጸደቀ ሲሆን በዚህም የብሄረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበበ ተቀባ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ፣ አቶ ጳውሎስ በላይ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም አቶ ጸጋው እሸቴ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም