ፖሊስ የፍርድ ቤቱን መጥሪያ ለማድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገለፀ

137

ግንቦት 16/2011 የፌዴራል ፖሊስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያዘዘውን የመጥሪያ ወረቀት ለእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ለማድረስ እንዲሰጠው ያቀረበው የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ።

በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ የተመሰረተባቸው 22 ሰዎች ዛሬ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ውስጥ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሸሻይ ልዑል መጥሪያ እንዲያደርስ ፍርድ ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ትዕዛዝ የተሰጠው ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓም ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ የደረሰው ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓም በመሆኑ፤ ይሕው የፍርድ ቤት መጥሪያም የሚሔደውም ወደ ትግራይ ክልል በመሆኑ ትእዛዙን ለመፈፀም ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በዚሁ መዝገብ ስር ክስ ከተመሰረተባቸው 26 ሰዎች ውስጥ 22ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሔደባቸው ነው።

በዛሬው እለትም አቃቢ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ አለኝ የሚለውን የሲዲ ማስረጃ በታዘዘው መሰረት ለፍርድ ቤቱና ለተከሳሾች አከፋፍሏል።

በሌላ በኩል ተከሳሾቹ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የደሞዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንደተቋረጠባቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ በማቅረባቸው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ በወንጀል ችሎት የማይታይ መሆኑንና በተከሳሾች የቀረበውም አቤቱታ ጉዳዩ በሚመለከተው አካል እንዲታይ ትእዛዝ ሰጥቷል።

በመጨረሻም ፖሊስ ተከሳሾቹን በአድራሻቸው አፈላልጎ መጥሪያውን እንዲያደርስ ተጨማሪ ጊዜ በመስጠት ለሰኔ 3 ቀን 2011 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም