በጀቱ ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ነው ...ዶክተር አብርሃም ተከስተ

117
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 የ2011  በጀት የተዘጋጀው አጠቃለይ  ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትርሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ገለጹ። የሀገሪቱ የቀጣዩ ዓመት በጀት 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ሚኒስትሩ የ2011 ረቂቅ በጀት በተመለከተ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። የመጪው ዓመት በጀት ከ2010 ዓ.ም ጋር ሲታይ የ12 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ያለፈውን የበጀት አፈጻጸምና የቀጣዩን ዓመት ረቂቅ በጀቱን ገለጻ  ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ በጀቱ የ2ኛውን እድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈጻጸምን፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ማስቀጠልን፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን፣ ዘላቂ ልማት ዘርፎችን እና የድህነት ቅነሳንና ወጪ ቅነሳን ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የ2011ዓ.ም የ2ኛው ዕድገትና ትራስፎርሜሽን 4ኛ ዓመት በመሆኑ በጀቱን ለማዘጋጀት አጠቃለይ የኢኮኖሚ ሁኔታው ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል። ሚኒስትሩ አክለውም መንግስት በቀጣዩ በጀት ዓመት ለታክስ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው የገለጹት። እነዚህን ታሳቢዎችና የውጭ ዕርዳታን መሰረት በማድርግም የ2011 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት ገቢ 254 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ታቅዷል ብለዋል ሚኒስትሩ። ይህም ከታክስ 211 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆነ ገቢ 24 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2010 ከታወጀው የተጨማሪ በጀት ጨምሮ ከዚህ ዘርፍ 34 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከውጭ ብድር የሚገኝ ሀብት የአጋር ድርጅቶች ድጋፍን ጨምሮ የፋይናንሱን ፍሰት በማየት ይህን የቀጥታ በጀት ድጋፍ እና የፕሮጀክት ዕርዳታ ሲሆኑ፤ ከድጋፉ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር እና ከፕሮጀክት የ16 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ይገኛል ተብሎ ተገምቷል። የወጪ በጀት ድልድልን በተመለከተም የፊስካል ፖሊሲና የ2ኛው ዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅዱ ቁልፍ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግቦችን እና የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦችን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ሚኒስትሩ። እንዲሁም የወጭ ቅነሳ፣ ወጭ ቁጠባ፣ አደጋ መከላከል እንዲሁም የዕዳ ክፍያንም መሰረት ያደረገ በጀት እንደሆነም ጠቁመዋል ሚኒስትሩ። ምክር ቤቱ ዶክተር አብራሃም ተከስተ የ2011 ረቂቅ በጀት በተመለከተ በሚያቀርቡት የበጀት መግለጫ ላይ በመወያየት ረቂቅ የበጀት አዋጁን ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ እንደሚመራም ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም