ኮንፍረንሱ የኦሮሞና አፋር ህዝቦችን አንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት ያጠናክራል ተባለ

95

ግንቦት 16/2011በአዳማ ከተማ የተካሄደው የግንኙነተና የሰላም ኮንፍረስ የኦሮሞና አፋር ህዝቦችን በልማት በማስተሳሰር አንድነታቸውንና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያጠናክር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ከአፋር ክልል የተወከሉት ሼህ ሙሐመድ ደረሳ ሙሴ እንደገለጹት ሁለቱ ህዝቦች በደም የተሳሳሩ ከመሆኑም በላይ  የሚጋሯቸው ባህላዊና ታሪካዊ ግንኙነት አላቸው።

“ህዝቡ ተለያይቶ መኖር አይችልም “ ያሉት ሼህ መሐመድ በአሁኑ ወቅት አንድነታቸውን በማጠናከር ለአካባቢውም ሆነ ለሀገር ሰላምና ልማት ቀጣይነት የድርሻቸውን ለመወጣት  ኮንፍረንሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያጠናክር ገልጸው በኦሮሚያ ክልል ለተደረገላቸው አቀባበልና መልካም መስተንግዶም አመስግነዋል።

 ህዝቡ ሰላሙን በመጠበቅና ወንድማማችነትን በማጠናከር ለሀገር ብልፅግና እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል የተወከሉት የሀገር ሽማግሌ አቶ ገመቹ ፎሌ ናቸው።

ኦሮሞከአፋር ጋር ወንድማማችነትና ጉርብትና ለማጠናከር ኮንፈረንሱ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

“ህዝቦችን ለማጋጨትና አንድነትን ለማዳከም የሚጥሩ ጥፋተኞችን በማጋለጥ ለህግ እንዲቀርቡ በትብብር እንስራለን” ብለዋል።

በክልሎቹ ደረጃ የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ የግንኙነት ስራዎች በአጎራባች ዞኖች ፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጌቱ ተገኑ የተባሉት የኮንፍረንሱ ተሳታፊበሰጡት አስተያየት “ ከአፋርና ከሌሎች ህዝቦች ጋር የተጀመረው የግንኙነትና የሰላም ኮንፍረንስ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ተደራሽ መሆን አለበት” ብለዋል።

ግጭት ቀስቃሾች ወደ መልካምተግባር መመለስ እንዳለባቸው ያመለከቱት አቶ ጌቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ዘላቂ ሰላም ፣ልማትና ፍትህ ማረጋገጥ በሚችሉበት ደረጃ ቢቀጥል እንደሚበጅ አስረድተዋል።

በኮንፍረንሱ የአፋርና ኦሮሞ ህዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።

በአዳማ ከተማየተዘጋጀው የሁለቱ ክልሎች ህዝባዊ  ኮንፍረንስ በአጎራባች ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የጋራ ልማትንና ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ አቅጣጫ በማመላከት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም