የበደሉትን ሕዝብና መንግስት ለመካስ እንደሚሰሩ በይቅርታ የተለቀቁ የህግ ታራሚዎች ገለጹ

141

ፍቼ ግንቦት 16/2ዐ11 በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ የበደሉትን ሕዝብና መንግስት ለመካስ እንደሚሰሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በይቅርታ የተለቀቁ የህግ ታራሚዎች ገለጹ ።

የክልሉ መንግስት በወሰነው መሰረት ይቅርታ የተደረገላቸው 317 የህግ ታራሚዎች ዛሬ ከዞኑ ማረሚያ ቤቶች ተለቀው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።

በይቅርታ ከተለቁት ታራሚዎች መካከል አቶ በፍቃዱ መገርሣ በሰጡት አስተያየት መንግስት በይቅር ባይነት ከማረማያ ቤት ወጥተው ወደ ቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ መፍቀዱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በቀሰሙት የእንጨት ሥራ እራሳቸውን በመቻል የበደሉትን ሕዝብና መንግስት ለመካስ እንደሚጥሩ ገልጸዋል፡፡

ቀሪ ሁለት ዓመት የእስር ጊዜ እያላቸው ይቅርታ እንደተደረገላቸው የገለፁት ደግሞ አቶ ደበሌ ሁንዴ ናቸው።

ከጥፋታቸው መማራቸውን አመልክተው በሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ በመደገፍ ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር እንዲጠናከር በሚደረገው እቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ይቅርታው እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

ወንጀል ፈፅመው ወደ ማረሚያ ቤት የገቡት በግዛቤ እጥረትና በእውቀት ማነስ እንደሆነ አምነው ሁሉም እራሱን ከወንጀል ድርጊት እንዲያርቅ እንደሚያስተምሩ ገልፀዋል፡፡

“በይቅርታው መካተቴ አስደስቶኛል “ ያሉት አቶ በሽር ለማ በበኩላቸው በመንግስት የተደረገላቸው ይቅርታ በፈፀሙት ወንጀል ይበልጥ እንዲፀፀቱ እንዳደረጋቸው አመልክተዋል።

ከህብረተሰቡ ጋር በሚቀላቀሉበት ወቅትም ይቅርታ በመጠየቅ ባላቸው ጉልበትና አቅም ሁሉ የበደሉን በመካስ በበጎ ስራ ስማቸውን ለመቀየር እንደሚጥሩም ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት የወንጀል አስከፊነትና ጣጣውን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በማስተማር ጥፋት እንዳይፈፅሙ በማስተማር ለማገዝ ዝግጁ ናቸው፡፡

ወይዘሮ ፈይፍቱ ባጫ በበኩላቸው በመነግስት የተደረገላቸው ይቅርታ ልጆቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማስተማርና ኑሮአቸውን ለማሻሻል የሚረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው በሚካሄድ የሰላምና የአንድነት ጉዞ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እድል የሚሰጣቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ገቢ ለማስገኘት የሚረዳቸውን የልብስ ስፌትና የባልትና ሞያ እንደቀሰሙም አመልክተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በወሰነው መሰረት ይቅርታ ተደርጎላቸው ዛሬ ከህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ከተደረጉት 317 የህግ ታራሚዎች መካከል 13 ሴቶች መሆናቸውን የዞኑ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ኢንስፔክተር አበበ መንገሻ አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በልዩ ልዩ ወንጀሎች በመሳተፍ በህግ ጥላ ስር ለነበሩ ከ7 ሺህ ለሚበልጡ ታራሚዎች በቅርቡ ይቅርታ ማድረጉ ይታወሳል።