ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኬንያ ያቋቋሙትን ቄራ ስራ በኢትዮጵያ የማስፋት ሃሳብ አላቸው

68

ግንቦት 16/2011 ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጋራ በኬንያ ያቋቋሙትን የ'ነኢማ የቁም እንስሳት እርድ ቄራ ሃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር' ስራዎችን በኢትዮጵያ የማስፋት ሃሳብ እንዳላቸው ገለጹ።
የ'ነኢማ የቁም እንስሳት እርድ ቄራ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር' ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ቦናያ ባካታ፤ የማህበሩን ስራዎች ወደ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ በማስፋት ቀጣናውን በዘርፉ የላቀ ለማድረግ ታስቧል።

እ.አ.አ በ2015 የተቋቋመው የ'ነኢማ የቁም እንስሳት እርድ ቄራ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር' በቀን ከሶስት ሺ እስከ አራት ሺህ የሚደርሱ በግና ፍየሎች በማረድ ስጋ ለመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እያቀረበ ይገኛል።

የማህበሩ አባላት በአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ ቀደም ብሎ በኬኒያ ውስጥ በየቤቱ በመሄድ የፍየልና በግ እርድ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም የስጋ ምርት ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌትና ኦማን እየላከ ሲሆን፤ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገበያ ለመቀላቀል የሚያስችለውን የብቃት ማረጋገጫ አግኝቷል።

በ500 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ (አምስት ሚሊዮን ዶላር) መነሻ ካፒታል የተቋቋመው ይህ ድርጅት አጠቃላይ ካፒታሉን ሁለት ቢሊዮን ሽልንግ አድርሷል።

ድርጅቱ ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች አልፎ ምርቱን ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችለውን የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ለማግኘት እየጣረ ነው።

እንደማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የብቃት ማረጋገጫውን ለማግኘት የሚያስችል ተቋማዊ የብቃት ፍተሻ በተመለከተ የጥራትና ደረጃ ፈታሽ አካላትን እያስገመገመ ነው።

ድርጅቱ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት ሰፊ ጥናት ማድረጉንና የባለሙያ ምክር ማግኘቱን የገለጹት ሚስተር ቦናያ፤ የኬንያ መንግስት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በኬንያ ውስጥ ከሚገኙ የቄራ ድርጅቶች  መካከል አንዱ ለመሆንና ስራውን ለማስፋፋት መቻሉን ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በመካከለኛው ምስራቅ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻሉትን ተሞክሮዎች በኢትዮጵያ በተመሳሳይ ተግባር ለተሰማሩ ድርጅቶች ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ያመለከቱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በኬንያ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እንደሚወያይበት ገልጸዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው፤ የነኢማ የቁም እንስሳት እርድ ቄራ ሃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር ብቻ ሳይሆን ሌሎች በኢንቨስትመንት መሰማራት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቷ ያለውን ዕድል እንዲያውቁ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኬንያ በተለያዩ የስራ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስኬታማ እየሆኑ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም