የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ

55

ግንቦት 16/2011የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በቡታጅራ ከተሞች ይካሄዳሉ።
ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከቀኑ ሶስት ሰአት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ  ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከቀኑ ሶስት ሰአት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌዴራል ፖሊስ ከጎንደር ከተማ ከቀኑ 8 ሰአት ከ30 ደቂቃ የሚጫወቱ ይሆናል።

ከነገ በስቲያ ድሬዳዋ ከተማ ከከምባታ ዱራሜ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ምክንያት በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ በመግለጹ ከምባታ ዱራሜ በፎርፌ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 አሸናፊ እንደሆነ ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይም ሳምንታት መርሃ ግብሮች ከድሬዳዋ ከተማ ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በውድድሩ ደንብ መሰረት የፎርፌ ውጤት እንደሚያገኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ24 ነጥብ ሲመራ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ21 መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ18 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ጎንደር ከተማ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።

በሌላ በኩል የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና ሶዶ ከተሞች ይካሄዳሉ።

ነገ አራት ኪሎ በሚገኘው የስፖርት ጅምናዚየም ሙገር ሲሚንቶ ከጣና ባህርዳር ከቀኑ ስምንት ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከቀኑ ሶስት ሰአት አዲስ አበባ ፖሊስ ከመዳወላቡ ዩንቨርስቲ ከረፋዱ አራት ሰአት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የሚጫወቱ ይሆናል።

  ሶዶ ላይ ከረፋዱ አራት ሰአት የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ መከላከያን ያስተናግዳል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ31 ነጥብ ሲመራ፣ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ26 ሙገር ሲሚንቶ በ20 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም