የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

219

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየምን በተሻለ አደረጃጀት መምራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

ረቂቅ ሰነዱ በባለስልጣኑ በኩል ዝግጅቱ ተጠናቆ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተልኮ ምላሹን እየተጠባበቁ እንደሆነ ተገልጿል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ42ኛ በኢትዮጵያ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረውን አለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በማስመልከት የፓናል ውይይት አዘጋጅቷል።

የባለስልጣኑ የሙዚየምና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ እንዳሉት፤ ብሄራዊ ሙዚየም ራሱን የቻለ የአሰራርና መመሪያ የሌለው በመሆኑ ከሌሎች አቻ ዓለም አቀፍ ብሄራዊ ሙዚየሞችና ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት ለመወሰን አስቸግሯል።

''ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗም ባለፈ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም የራሱ አሰራርና መመሪያ ያለው ብሄራዊ ሙዚየም አልነበራትም'' ብለዋል።

በመሆኑም ያሉትን ቅርሶች ለዓለም ለማስተዋወቅና በተሻለ አሰራር ሙዚየሙን ለማዘመንና የአንድ ሙዚየም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊይዘው የሚገባው መዋቅር እንዲካተትበት ለማድረግ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ብሄራዊ ሙዚየሙ በመዋቅሩ ከነበሩት የኤግዚቢሽን አዘጋጅና አስጎብኝዎች በተጨማሪ ብቁ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያ፣ የራሱ ዳይሬክተር፣ የገበያና እንክብካቤ ጉዳዮች በረቂቁ መካተቱን አቶ ኤፍሬም ጠቁመዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍሰሃ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ቅርስ በአግባቡ ለመጠቀም ግልጽ አሰራር መከተል እንዳለባት ተናግረዋል።

መንግስት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪስት መስህብ በመረዳት ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ''ቅርሶቻችንን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል አሰራሮችና መመሪያዎችን መፈተሽ ይገባል'' ብለዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መጎልበት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን "ሙዚየሞች በባህል ማዕከልነት ለትውፊቶቻችን ቀጣይነት የሚጫወተው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከግንቦት 10 እስከ 17 ቀን 2011 ዓ.ም እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም