የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወያዩባቸውን አጀንዳዎች አጸደቁ

64

አዲስ አበባ   ግንቦት 16/2011  የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ የሚወያዩባቸውን አጀንዳዎች ቅደም ተከተልና ለአወያይነት የተጠቆሙ ግለሰቦችን ዝርዝር አጸደቁ።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ በነበራቸው ውይይት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአወያይነት የተጠቆሙ ግለሰቦችን ዝርዝርና ለውይይት የቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተዋል።

ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት የቀረቡ አጀንዳዎች በቅደም ተከተላቸው መሰረት በሶስት አማራጮች ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የቀረቡ አጀንዳዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጉዳይና ምርጫ ቦርድን የተመለከተ፣ ምርጫ 2012 እና አካባቢያዊ ምርጫ፣ ከአገራዊ መግባባት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ህገ መንግስትና ፌደራሊዝም፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን የማሻሻል እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ናቸው።

ፓርቲዎቹ ቅድሚያ ሰጥተን መወያያት አለብን ብለው ባቀረቧቸው አጀንዳዎች ላይ በቀረበው አማራጭ መሰረት ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

አማራጮችን ለመወሰን  ለመስማማት  ተቸግረው የነበረ ቢሆንም   ባደረጉት  ውይይት  ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸውን አጀንዳዎች ይዟል ያሉትን አማራጭ አንድን ማስተካካያ በማድረግ አጽድቀዋል።

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይን ፣ ምርጫ ቦርድን ፣ ምርጫ 2012 እና አካቢያዊ ምርጫ የተመለከተና  ሌሎች አጀንዳዎችን በቅደም ተከተል ለማየት ማሻሻያ አድርገው ተስማምተዋል።

የቀረቡት አጀንዳዎች ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረግ ድጋፍ፣ ስለምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ የመገናኛ ብዙሃን ህግ ማሻሻያ፣ ምርጫ መራዘምን በተመለከተ፣ ሰንደቅ አላማ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ እና ሌሎች የተለያዩ ጉዳዮችን በስራቸው ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወያያ አጀንዳዎችን ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ተሳትፎዎች አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም