የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ

79

ግንቦት 16/2011የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልልና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ።
ነገ በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ፣ በጅማ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋር ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ እና በሀዋሳ ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከደቡብ ፖሊስ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በፕሪሚየር ሊጉ ከአንድ እስከ ሶስት የሚገኙት ክለቦች ፋሲል ከነማ መቐለ ሰብዓ እንደርታና ሲዳማ ቡና ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ ዋንጫው ለማንሳት በሚያደርጉት ፉክክር ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሚባል ነው።

ነገ በአሰላ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ።

ሀዋሳ ጨዋታውን በሜዳው ማድረግ የነበረበት ቢሆንም ሀዋሳ ከተማ አንድ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታውን እንዲያደርግ ቅጣት የተጣለበት በመሆኑ ጨዋታው በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ተወስኖ ነበር።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ አካላት ለጨዋታው ሃላፊነት እንደማይወስዱ በማሳወቃቸው ምክንያት ጨዋታው ወደ አሰላ ስታዲየም እንደተሸጋገረ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከነገ በስቲያ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።

በክልል ከተሞች በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ፣ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከደደቢት እና በሽሬ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከመከላከያ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት የሚጫወቱ ይሆናል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ፋሲል ከነማ በ49 ነጠብ ሲመራ፣ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ48 ሲዳማ ቡና በ46 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 15 ግቦች ሲመሩ፣ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ12 የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ11 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም