ህገ-መንግስቱ ባለፉት ዓመታት ለተመዘገቡ ስኬቶች ምሰሶ ነው…ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

107

መቀሌ ግንቦት 16/2011 ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በሃገሪቱ ለተመዘገቡት ድሎች ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

የፌዴራል፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች የአፈጉባኤዎች የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል።

ምክትል ርዕሰመስተዳደሩ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ህገመንግስታዊ ስርዓቱ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ከተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ባለፈ ለዲሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ግንባታ መጎልበትም ማገዙን ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ብሄር ተኮር ጥቃት ፣ የዜጎች መፈናቀልና ህገመንግስታዊ ጥሰቶች መታየታቸውን ዶክተር ደብረጽዮን አስታውሰዋል።

“ችግሮቹ ህገመንግስቱንና የፌዴራል ስርዓቱን በማይቀበሉ ሃይሎች አቀነባባሪነት የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት ነው” ብለዋል።


የሀገራችን ህገመንግስት ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፣ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና ታሪካቸውን እንዲያሳድጉ መሰረት የጣለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ናቸው።

ህገመንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱ በቀረፃቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም የሀገራችን ህዝቦች ከድህነት ጋር እንዲፋለሙ በማድረግ ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ፈጣን እድገት በማስመዝገብ እንድትታወቅ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በየደረጃው ያሉት የህዝብ ምክር ቤቶች የሚያካሂዱት የምክክር መድረክ በህገ-መንግስቱ የተሰጧቸውን ተልእኮዎች በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል አቅም ለመገንባትና ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የሚያግዝ መሆኑንም አፈ-ጉባኤው ጨምረው አስረድተዋል።

የምክር ቤቶች አባላት ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለህገ-መንግስቱ ተልእኮ መሳካት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም አቶ ታገሰ ያሳስበዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎችን ጨምሮ የሁሉም ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች አፈ ጉባኤዎችና ምክትል አፈ ጉባኤዎች እንዲሁም ቋሚ ኮሚቴዎች ተሳታፊዎች ሆነዋል።

ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው የህዝብ እንደራሴ ምንነትና ፋይዳው፣የህዝብ ተወካዮች ተልእኳቸውን ለመወጣት ማድረግ ስላለባቸው ሃላፊነት እንዲሁም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሰራር በተደረጉ ጥናቶችና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ለሁለት ቀናት ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም