“ ፊቼ ጫምባላላ ” በይቅርታና አብሮነት ሊከበር እንደሚገባ ተመለከተ

67

ሀዋሳ ግንቦት 16/2011ዓ.ም የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ “ ፊቼ ጫምባላላ ” የዕርቅና ሠላም በዓል በመሆኑ ይህንኑ አኩሪ ባሀል በሚያንጸባረቅ ይቅርታና አብሮነት ሊከበር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ከዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ጋር በመተባበር"ፊቼ ጫምባላላ የዕርቅና የሰላም መገለጫ ነው " በሚል ሀሳብ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ተካሄዷል፡፡

በዚህ ወቅት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫዊቻ እንደገለጹት “ ፊቼ ጫምባላላ ” ጥንት ዘመናዊ ዕውቀት ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ የብሔሩ የዘመን አቆጣጠር ልሂቃን በሆኑት “ አያንቱዎች ” አማካይነት የዘመን መለወጫ ጊዜን በማስላት ጥበብን ለትውልድ ሲያስተላልፍበት የቆየ በዓል ነው፡፡

በዓሉ የሲዳማ ህዝብ አቃፊነት መገለጫም ጭምር በመሆኑ ከሌሎች ብሔር ብሄረሰቦች ጋር በአብሮነት የሚያከብረው እንደሆነም አስረድተዋል ፡፡

በሲዳማ ዘንድ ዕርቅ ሳያርጉ “ ፊቼ ጫምባላላ ”ን ማክበር የተከለከለ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ቃሬ" በዓሉን በዕርቀ ሠላምና አብሮነት ልናከብር ይገባል "ብለዋል ፡፡

የዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘው በበኩላቸው በዓሉ ከዘመን መለወጫነት ፋይዳው ባሻገር በርካታ ባህላዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያላቸው እሴቶችን በውስጡ መያዙን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ ሠላም ፣ ዕርቅና መከባበር እንዲሰፍን የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎችን በማካሄድ ይበልጥ እንዲተዋወቅና ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

እየተካሄደ ያለው የፓናል ውይይት የሥራው አንዱ አካል እንደሆነም አብራርተዋል ፡፡

ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የማህበራዊ አንትሮሎጂ ተመራማሪ ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ እንዳመለከቱት በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህል ውስጥ የሚገኙ ለሰላምና መቻቻል ጉልህ ሚና ያላቸው እሴቶች ይኖራሉ።

ሆኖም ለሀገር በቀል ዕውቀት ተገቢው ትኩረት ተነፍጎ በመቆየቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

የባህላዊ እሴቶች ሀገራዊ ፋይዳ ለማጉላትም በቂ ጥናቶች ሊካሄዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ዶክተር አምባዬ “ ፊቼ ጫማባላላ ” የሲዳማ ብሔር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ለአለም ያበረከቱት የማስታረቅ ፤ ሌላውን የማካተትና የመከባበር መሠረታዊ ፅንሰ ሀሳቦችን የያዘ በዓል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

"አሁን ላይ ከትውልዱ እየተሸረሸሩ ያሉትን የሠላም እሴቶች ጠብቆ ለማቆየት በዓሉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ በሠላም ማክበር ይገባል "ብለዋል፡፡

ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታሪኩ ሾና እንደተናገሩት በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት ፤ ተራርቀው የቆዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት ሰላምና ፍቅርን የሚሰብክ ነው፡፡

“ ፊቼ ጫማባላላ ” ሁሉም ተጠራርተው በአንድነት የሚያከብሩት እንጂ የጥል አለመሆኑን የገለፁት አቶ ታሪኩ "በዓሉ የሁሉም ብሔር ብሄረሰቦች እንደመሆኑ ያሉትን የሰላም እሴቶች መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው "ብለዋል ፡፡

ሌኛላው አስተያየት ሰጪ አቶ ወንድሙ ብሩ የበዓሉ ዕለት የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ጭምር ሠላም የሚውሉበትና ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚደረግበት እንደሆነ ተናግሯል፡፡

የበዓሉ እሴት የሆነውን ሠላም መጠበቅ የሁላቸውም ድርሻ በመሆኑ አከባበሩ የሠላም ሆኖ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ ትናንት በተካሄደው የፓናል ውይይቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የዘንድሮው የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ “ ፊቼ ጫምባላላ ” በዓል ግንቦት 22 እና 23/2011ዓ.ም. እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም