በምስራቅ ጎጃም ዞን በ260 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየተሰራ ነው

77

ግንቦት 16/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን በ260 ሄክታር ማሳ የበቆሎ ተክል ላይ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመስኖ ልማት የሥራ ሂደት ባለሙያ አቶ ሞላ ሰውነት ለኢዜአ እንደገለጹት ተምቹ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተከሰተው በማቻከል፣ በአንደድ፣ በሰዴ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በጎዛምን እና በደብረ ኤሊያስ ወረዳዎች በመስኖ እየለማ ባለ የበቆሎ ሰብል ላይ ነው።

ተምቹ በሰብሉ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በግብርና ባለሙያዎች እገዛ የአርሶ አደሩ ጉልበትን በመጠቀም በለቀማና ኬሚካል በመርጨት የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ቀናት በተሰራ የመከላከል ሥራም 48 ሄክታር ላይ የነበረውን ተምች በለቀማ እንዲሁም 129 ሄክታሩን ኬሚካል በመርጨት የመከላከል ሥራ ተሰርቷል።

እንደባለሙያው ገለጻ በመከላከል ስራው ከ600 በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለስራውም 360 ሊትር ኬሚካል ክልል ግብርና ቢሮ ቀርቦ 130 ሊትሩ ጥቅም ላይ መዋሉን ነው የገለጹት፡፡

"ተምቹ አጋጣሚ እስከሚያገኝ እራሱን ደብቆ የመቆየት ባህሪ ስላለው በመኽሩ በሚለማ የበቆሎ ተክል ላይ እንዳይተላለፍ እና ወደሌሎች የመስኖ አካባቢዎችም እንዳይዛመት በለቀማ ለመግደል የዘመቻ ሥራ ይሰራል" ብለዋል።

የአነደድ ወረዳ የየዳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አገኘሁ በቀለ እንዳሉት በግማሽ ሄክታር የበቆሎ ሰብላቸው ላይ የተከሰተውን ተምች በለቀማና በኬሚካል እየተካላከሉት መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው አመትም በአካባቢው ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

የማቻከል ወረዳ የየውላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደምስ ምንይችል በበኩላቸው ሁሉን አውዳሚ ተምች በመስኖ ካለሙት ሩብ ሄክታር የበቆሎ ማሳቸው ላይ መከሰቱን ነው የተናገሩት።

ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ተከስቶ ፈጥነው መከላከል ባለመቻላቸው ጉዳት ያደረሰባቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ከእዚያ ትምህርት በመውሰድ ዘንድሮ ወዲያውኑ መቆጣጠር መቻላቸውን አስረድተዋል።

በዞኑ በአንደኛና በሁለተኛ ዙር መስኖ ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ መልማቱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም