ምክር ቤቱ በመተከል ዞን የድምጽ አልባ መሣሪያ ዝውውር ገደብ ጣለ

101

አሶሳ ግንቦት 16 /2011 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጸጥታ ምክር ቤት በመተከል ዞን የድምጽ አልባ መሣሪያ ዝውውር እገዳ እንዲደረግበት ወሰነ ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት ውሳኔውን ያስተላለፈው በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም  በዞኑ ግጭት በተከሰተባቸውም ሆነ በየትኛውም አካባቢዎች መሣሪያዎች እንቅስቃሴ  ተከልክሏል፡፡

እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው አካላት በስተቀር የሚሊሺያ፣ የቀበሌ ታጣቂዎችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ምክር ቤቱ ገደብ ጥሏል፡፡

እንዲሁም ክልሉ ከአማራ ክልል በሚዋሰንባቸው ድንበሮች አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ብቻ የጦር መሣሪያ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ፈቅዷል።

 የክልሉ ልዩ ኃይልም ሆነ መደበኛ ፖሊስ የጦር መሣሪያ ይዘው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ  በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በዳንጉር፣ ማንዱራ፣ ፓዌ ና ድባጤ ወረዳዎች የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ውሳኔውን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ምክር ቤቱ አዟል፡፡

በአካባቢው የተከሰተውን ግጭት በማስወገድ የህግ የበላይነት ለማስከበር የተጀመረውን ጥረት ከዳር እንዲደርስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክቷል።

ለክልሉ ሠላም የክልሉ ሕዝብ ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበት የጠቀሰው መግለጫው፣ በዞኑ በግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም