የአማራ ክልል ህዝብ ለሃገርና ለክልሉ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይገባል…ዶክተር አምባቸው መኮንን

81

ግንቦት 16/2011 የአማራ ህዝብ ለክልሉና ለሃገሪቱ በዘላቂነት በሚጠቅም ስራ ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን አሳሰቡ።
ርዕሰመስተዳደሩ ዛሬ ከባህርዳር ከተማ ህዝብ ጋር በመልካም አስተዳደር ፣በልማትና በሰላም ጉዳዮች እየተወያዩ ነው።

በዚህ ወቅት እንዳሉት አዲሱ የክልሉ አመራር የአማራን ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ችግሮችን ለይቶ እየሰራ ይገኛል። 

አመራሩ ለክልሉ ህዝብ መብት መከበር በሚያደርገው ጥረትም ሁሉም በአንድ ሃሳብ ሊደግፍና ሊያግዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም ሊመለሱ የሚችሉት ከአመራሩ ጎን በመሆን ማገዝና መደገፍ ሲችል እንደሆነም አስረድተዋል።

“ስለሆነም እንዲመለሱለት የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎች በሃሳብ ሳይከፋፈል አንድ ሆኖ በጋራ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አመራሩን መታገልና ማታገል ይኖርበታል”ብለዋል።

የውይይቱ አላማም ህዝቡ የሚሰማውን ሃሳብ የመቀበልና በቀጣይ ለመፍትሔው በጋራ መስራት እንዲቻል ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል። 

በውይይቱ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች የሃማኖት አባቶች የሃገር ሽማግሌዎች ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም