ዩኒቨርሲቲው በትምህርትም ሆነ በተግባር ልምምድ ያልተገኙ ተማሪዎች ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ወሰነ

87

ግንቦት 16/2011 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትምህርትም ሆነ በተግባር ልምምድ ያልተገኙ የስድስተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪዎች ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሥራ እንዲመለሱ መወሰኑን አስታወቀ፡፡ 

ይቅርታ አንጠይቅም ያሉ የዩኒቨርሲቲው የሕክምና ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በመውጣት ላይ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ይቅርታ ጠይቀው እንዲመለሱ የፈቀደላቸው ላለፉት 20 ቀናት  ከትምህርትና  ከተግባራዊ ልምምድ  ተለይተው ለነበሩ  የሕክምና ተማሪዎች ነው።

ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎቹ የቀረቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ  ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ፣ በዚሀም  ሰባት አባላት ያሉት የሲኒየር ሐኪሞች ኮሚቴ በማዋቀር እንዲሁም በሙያ ማህበሩ ጭምር ከተማሪዎች ተወካዮች ጋር ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ መወያየቱን ተናግረዋል፡፡

ምላሽ እንዲያገኙ ከተደረጉ ጥያቄዎች መካከልም ናሙና የሚያመላልሱ ሠራተኞች ቅጥር እንዲፈጸም፣ የላቦራቶሪ ክፍል የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥና የኢንተርን ሐኪሞች የማረፊያ ክፍል ማሟላት ይገኙባቸዋል ብለዋል፡፡

የኢንተርን ሐኪሞች የ36 ሰዓት የሥራ ጫና ወደ 24 ሰዓት ዝቅ እንዲልና ጉልኮ ሜትርን ጨምሮ ሌሎች ያልተሟሉ የሕክምና መሳሪያዎች እንዲሟሉ ጥረት መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የተማሪዎቹ የሕክምና ሥነ ምግባርን በመጣስ በሽተኞች እንዲጉላሉ በማድረግ ትምህርትና የተግባር ልምምድ በማቆም በፈጸሙት የዲስፕሊን ግድፈት ሴኔቱ ግንቦት የበደሏቸውን ታማሚዎች ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ትምህርትና ሥራ ገበታ እንዲመለሱ  ወስኗል ብለዋል፡፡

ይቅርታ የማይጠይቁ ከሆነ ግን፤ ለአንድ ዓመት ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ መወሰኑንም ዶክተር አስራት  አስታውቀዋል፡፡

ተማሪዎቹ ጥያቄ አግባብነት ያለው ቢሆንም፤ ጥያቄው የቀረበበት መንገድ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማርና የሕክምና አገልግሎት ያስተጓጎለ ነው ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስማማው አጥናፉ ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሕክምና ኮሌጅ የስድስተኛ ዓመት ተማሪ ዶክተር አብይ ኃይሌ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባለፉት ዓመታት በርካታ በደሎችን የፈጸመ አካል በመሆኑ ይቅርታ አንጠይቅም ብሏል፡፡

''የታካሚዎቻችን ድምጽ ይዘን ነው ጥያቄ ያቀረብነው፤ ሕዝባችንን አስከፍተን ከሆነ ግን ሕዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነን'' ሲል ተናግሯል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተላለፈው ውሳኔ ባይገለጽልንም ፤ በርካታ የኮሌጁ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በመውጣት ላይ እንደሆኑም አስታውቋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በመደበኛ ትምህርታቸውና ከተግባር ልምምድ ያልተገኙት የሕክምና ተማሪዎች ቁጥር 252 ሲሆን፣ እስከ ትናንት ድረስ ግማሽ ያህሉ ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም