ለባህላዊ የእርቅና የሽምግልና ስርዓት ትኩረት አለመሰጠቱ ግጭትን አባብሷል

163

ግንቦት 15/2011 በኢትዮጵያ የእርቅና የሽምግልና ስርዓት ሰዎች በእርስ በርስ ግንኙነት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን የሚፈቱበት ቢሆንም ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑን ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚጠቅሱት።
የእርቅ ስርዓቱ ግለሰቦች በመካከላቸው ጥቃቅን አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ተባብሰው የከፋ ጥፋት እንዳያደርሱ በሰከነ መንፈስ ተወያይቶ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከመደበኛ የፍርድ ስርዓት ጎን ለጎን ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነም ይነገራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች በዚሁ ስርዓት መፈታት ሲገባቸው በተቃራኒው ጥቃቅን ግጭቶች ተባብሰው በመቀጠል ለሰው ህይወት መጥፋት፣ ለንብረት መውደምና ለዝርፍያ ምክንያት እንደሆነም ይጠቀሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አቶ አለምነው ደሴ በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት የዜጎችን አብሮነት ለማጠናከርና ግጭቶችን ለመከላከል መንግስት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ጎን ለጎን ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በተወሰነ ደረጃ መጠቀም ቢታይም በቂ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።

በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የዜጎች ሞትና መፈናቀል በብዛት ይስተዋላል ያሉት አቶ አለምነው፤ ችግሮቹ በለውጥ ጊዜ የሚያጋጥሙ ቢሆንም፤ ተባብሰው እንዲቀጥሉ ያደረገው ሀገራዊ የጋራ እሴቶች በመሸርሸራቸው ነው ይላሉ።

እሴቶቹን “መንግስት ትኩረት ነፍጓቸዋል፣ እውቅናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሸርሽሯል፤ ስለሆነም ትውልዱ እየረሳቸው መጥቷል” ያሉት መምህር አብዲሳ አጋ በበኩላቸው፤ ስርዓቱ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ቢቀጥል ኖሮ ዛሬ ችግሮች በቀላሉ ይፈቱ እንደነበር ይገልጻሉ።

ድሮ ፀብ ሲኖር ሳይባባስና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ አባቶችና እናቶች ቁጭ ብለው በአገር ባህል የተበደለን ክሰው የበደለን ደግሞ ወቅሰው፤ ይቅር በማባባል ወደ ቀደመ ግንኙነታቸው ይመልሱ የነበረው ሁኔታ እየደበዘዘ መምጣቱንም ይናገራሉ።

ባህላዊ እሴቶች በወጉ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው በሰዎች መካከል ለዘመናት የዘለቀው የመቻቻልና የሽምግልና ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት ወይዘሮ ቅድስት አበጋዝ፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ታላላቆቻቸውን እንዲያከብሩና የሚነገራቸውን እንዲቀበሉ አድርገው ባለመቅረፃቸው ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ፤እያንዳንዳቸው የየራሳቸው አገር በቀል የፍትህ፣ የህግና የአስተዳደር ባህላዊ የግጭት መፍቻ እሴቶች አሏቸው፡፡
እነዚህ ስርዓቶች በተለያዩ ቋንቋዎች የተለያየ ስያሜ ይኑራቸው እንጂ የመጨረሻ ግባቸው ግጭትን በማስወገድ አብሮነትን ማጠናከር ነው፡፡

የሀገሪቱ ህዝቦች እነዚህንና ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን ተጠቅመው በማህባራዊ መስተጋብሮቻቸው የሚያጋጥማቸውን መቃቃሮች በማስወገድ፤ እርስ በእርስ በመፈቃቀር፣ በመከባበርና በመቻቻል በአብሮነት ዘመናትን አሳልፈዋል።

በሀገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶችን አስወግዶ አብሮነትን በማጠናከር ና የህዝቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ጎን ለጎን ባህላዊ የሽምግልና ስርዓቶችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም