በጋምቤላ ከተማ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እየተሰራ ነው

102
ጋምቤላ ግንቦት 30/2010 በጋምቤላ ከተማ በክረምቱ ወራት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አስታወቁ፡፡ በከተማዋ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን የጎርፍ አደጋና የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ችግር ለማቃለል ከ41 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ቺቢ ቺቢ ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምት ወራት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይና 12 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ እየተካሄደ ነው። የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታ በተለይም በከተማዋ አካባቢ ካሉ ተራራማ ቦታዎች   የሚነሳውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የጎርፍ አደጋ በሚከሰትባቸው የከተማዋ አካባቢዎች የቦይ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከከተማዋ ህብረተሰብ ጋር በመተባበር የተደፈኑ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮችን የማጽዳትና በየአካባቢው የሚጣል ቆሻሻን ማህብረሰቡ እንዲቆጣጠር የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተሰሩ የማፋሰሻ ቦዮች ግንባታና አካባቢን የማጽዳት ሥራዎች በከተማዋ ይከሰት የነበረውን የጎርፍ አደጋ በመጠኑም ቢሆን ማቃለል መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ አሁን በመሰራት ላይ ያለው የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ በከተማዋ ያለውን የጎርፍ ስጋት እንደሚያቃልልም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ያሉት አቶ ቺቢ ህብረተሰቡም አካባቢውን በባለቤትነት ስሜት በመቆጣጠር  የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮችን በማጽዳት ረገድ ያሳየውን ትብብር ሊያጠናክር እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ የከተማዋ መሰረተ-ልማት ማስፋፊያ አስተባባሪ አቶ ትግዕስቱ በፈቃዱ እንደገለጹት የማፋሰሻ ቦዩ በአካባቢው ሊከሰት የሚችለውን ጎርፍ ግምት ውስጥ በማስገባት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ የሚካሄደው የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 70 ከመቶ በላይ መጠናቀቁ ጠቁመው በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 12 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የኮብል እስቶን ንጣፍ ሥራና ወደ አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማዋ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በየአካባቢው ያለውን የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮችን በማጽዳት የበኩላቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የ04 ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ኝግዎ ኡባንግ በሰጡት አስተያየት በክረምት ወቅት ሊከሰት ሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በቀበሌያቸው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጽዳት ዘመቻ ማካሄዳቸውንና በቀጣይም ችግሩን ለማቃለል የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡ የጎርፍ አደጋው በየአመቱ ያስቸግራቸው እንደነበርና ዘንድሮ የተሰራው የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ችግሩን እንዳቀለለላቸው የገለፁት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ተስፉ በላቸው ናቸው፡፡ አቶ ጌታቸው ፉንጄ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት እየተሰራ ያለው የማፋሰሻ ቦይ ጠባብ በመሆኑ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ አይፈታውም የሚል ስጋታት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም