በመጪው ቅዳሜ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአፍሪካ ቀን ይከበራል

123

ግንቦት 15/2011 በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተናጋጅነት የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም የአፍሪካ ቀን ይከበራል።
በየዓመቱ የሚከበረው የአፍሪካ ቀን ዓላማ በአፍሪካውያን መካከል በህብረት መስራትና አንድነትን በማጠናከር የአህጉሩን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ቃል ኪዳን መግባት ነው።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዓሉን እንዲያስተናግድ የተመረጠው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጀምሮ ለህብረቱ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ነው።

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከፀረቅኝ አገዛዝ ትግል ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አህጉሩን እየተፈታተኑ የሚገኙትን የሰላምና ፀጥታእንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ትግል ጉልህ አስተዋጽኦ አላት።

በኬንያ የሚከበረውን የአፍሪካ ቀን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መቀመጫቸውን ናይሮቢ ያደረጉ የአፍሪካ አገሮች አምባሳደሮች አገሪቷ ለአህጉሩ እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦን ከግምት በማስገባት መምረጣቸውን አስረድተዋል።

በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበርም ኢትዮጵያ የምትመራው የዝግጅት ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር መለስ፤ ''በኮሚቴ ውስጥ የሁሉም አገሮች ተወካዮች በአባልነት እየተሳተፉ ይገኛሉም'' ብለዋል።

ቀኑ አፍሪካውያን ባህላቸውን፣ አገራዊ እሴቶቻቸውንና ገጽታቸውን የሚያስተዋውቁበትና እርስ በርስ ተሞክሮ የሚለዋወጡበት መድረክ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደር መለሰ ገለጻ፤በአፍሪካ ቀን በአፍሪካ አገሮች መካከል በህብረት ለመስራትና የአህጉሩን በጎ ገጽታ ለዓለም ማስተዋወቅ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል።

በመድረኩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት፣ በአህጉሩ መጻዒ ዕድልና ተግዳሮት ላይ ምክክር በማድረግ አፍሪካውያን የጋራ ቃል ኪዳን በመግባት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ጭምር እንደሆነም አምባሳደር መለስ አብራርተዋል።

መድረኩ አፍሪካውያን በአንድ መድረክና በአንድ ቦታ ከሚሰባሰቡበት አጋጣሚዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደሩ፤ የባህል ዲፕሎማሲ የሚካሄድበት ቀነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ቀኑ በኤምባሲው ሲከበር በኬንያ ያሉ የአፍሪካ አገሮች ኤምባሲዎች ባህላቸውን ለዕይታ በማቅረብ እንደሚያስተዋውቁም ገልጸዋል።

በየዓመቱ በጎርጎርሳውያን አቆጣጠር ግንቦት 25 የአፍሪካ ቀን  መከበር የጀመረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አሁን የአፍሪካ ህብረት) በ1963 (እአአ) መመስረቱን ተከትሎ ነው።

ቀኑ በአፍሪካ አገሮችና በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ አገሮች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም